የአውሮፓ ህብረት ለአልዛይመር በሽታ የሚሰጠውን 'አዱካኑም' የተሰኘ አዲስ መድሃኒት እንዳይሰጥ ከለከለ
ብሪታንያ የአውሮፓ መድሃኒቶች ውሳኔ "አልዛይመር ላለባቸው ሰዎች በጣም የሚያሳዝን ነው" ብላለች
በአውሮፓ 8 ሚልዮን የሚሆኑ የአልዛይመር ሰለባዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ
በአውሮፓ ህብረት የአውሮፓ መድሃኒቶች ኤጀንሲ ለመርሳት በሽታ /አልዛይመር/ የሚሰጠውን 'አዱካኑም' የተሰኘ አዲስ መድሃኒት እንዳይሰጥ ከለከለ፡፡
ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የተገኘው አዲሱ የአልዛይመር መድሃኒት ከብዙ ክርክር በኋላ ባለፈው ወርሃ ሰኔ በአሜሪካ ተፈቅዶ በመድሃኒትንት ሲወሰድ የቆየ ነው ተብሏል፡፡
በወቅቱ በርካታ ተመራማሪዎች አዲሱ መድሃኒት አልዛይመር ባለባቸው ሰዎች አዕምሮ ላይ የሚገኘውን አምይሎይድ የተሰኘና በሰዎች አእምሮ ችግር የሚፈጥረውን ፕሮቲን ኢላማ ያደረገ ቢሆንም፤ ብዙ ጥቅም እንደሌለው ሲገልጹ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም የአውሮፓ ህብረት መድሃኒቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል መከልከሉ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡የመድሃኒቱ ባለቤት ባዮጂን ኩባንያ፤ የአውሮፓ መድሃኒቶች ኤጀንሲ መድሃኒቱን በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ዳግም እንዲመረምረው ጥያቄ አቅርቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ መድሃኒት የህክምና አማራጭ ለሌላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የአልዛይመር ሰለባዎች ዕድል የፈጠረ እንደመሆኑ በመከልከሉ ማዘናቸውን በርካታ የበጎ አድራጎት ማህብራት ግልጿል፡፡
በአውሮፓ 8 ሚልዮን እንዲሁም በብሪታንያ ብቻ 1 ሚልዮን የሚሆኑ የአልዛይመር ሰለባዎች መኖራቸውንና ይህም እንደፈረንጆቹ በ2050 በእጥፍ ሊጨምር እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡
በእንግሊዝ የአልዛይመር ምርምር ማእከል ዋና ስራ አስኪያጅ ሂላሪ ኢቫንስ፡ የአውሮፓ መድሃኒቶች ውሳኔ " አልዛይመር ላለባቸው ሰዎች በጣም የሚያሳዝን ነው" ብሏል፡፡
የመድሃኒቱ አምራች ባዮጂን ኩባንያ መድሃኒቱን የተመለከተ ተጨማሪ ጥናት እያደረገ መሆኑንም ጠቁሟል ሂላሪ ኢቫንስ፡፡ የመርሳት በሽታ/አልዛይመር/ ለሌሎች በርካታ በሽታዎች ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል፡፡