የኢትዮጵያ ቡና ንግድ በሀውቲ ታጣቂዎች ምክንያት ለሶስት ቀናት ተስተጓጉሎ ነበር ተባለ
ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ብታቅድም 82 በመቶው ብቻ መሳካቱ ተገልጿል
ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ኢትዮጵያ ቡናዋን ወደ 65 ሀገራት እንደላከች አስታውቃለች
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀይ ባህር ላይ ባደረሱት ጥቃት የኢትዮጵያ ቡና ንግድ ለሶስት ቀናት ተስተጓጉሎ ነበር ተባለ፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በ2016 በጀት ዓመት የውጪ ንግድ አፈጻጸም ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንዳሉት ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው 2016 በጀት ዓመት ውስጥ 350 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ነበር ብለዋል፡፡
ይሁንና አፈጻጸሙ 298 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደተገኘ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ሀገራት የምትልከው ቡና በቀይ ባህር በኩል በመሆኑ እና የሀውቲ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት ምክንያት መስጓጎል ገጥሞት እንደነበርም ተገልጿል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ኤምሲ መርከብ በኩል ወደ አውሮፓ ሀገራት በመጓጓዝ ለይ እያለ በሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት ምክንያት የቡና ንግድ እስከ ሶት ቀናት ድረስ በመስተጓጎሉ ምክንያት ኢትዮጵያ ከቡና ንግድ ማግኘት የነበረባትን ገቢ እንዳታገኝ አድርጓል፡፡
የሀውቲ ታጣቂዎች በቀጣይ የቡና ንግድ ላይ ስጋት ሊደቅኑ እንደሚችሉ፣ ነጋዴዎች ምርቶች በወደቦች ላይ ሲቆዩ ለተጨማሪ ወጪ እንዲሁም ይህን ሽሽት ቡናን በአየር ትራንስፖርት ሲልኩ ላልተፈለገ ወጪ ሊዳርጋቸው እንደሚችልም አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት የቡና ምርቶቿን ወደ 65 የዓለማችን ሀገራት ልካለች የተባለ ሲሆን ከተላከው ጠቅላላ ቡና ውስጥ 21 በመቶው ወደ ሳውዲ አረቢያ እንደተላከ ተገልጿል፡፡
አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቤልጂየም፣ ቻይና፣ ጃፓን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ከላከችባቸው ዓለማችን ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡