የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት ሊያቋቁም መሆኑን አስታወቀ
በይርጋጨፌ ይገነባል የተባለው ይህ ኢንስቲትዩት ከዲላ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር ይቋቋማል ተብሏል
ኢንስቲትዩቱ 2 ቢሊዮን ብር ይፈጃል የተባለ ሲሆን ቡና አምራቾች እና ላኪዎች በሚያዋጡት ገንዘብ እንደሚገነባ ተገልጿል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት ሊያቋቁም መሆኑን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር የቡና ስራ እና ንግድ ሳይንሳዊ አሰራርን ተከትሎ እየተሰራ እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) ለአልዐይን እንዳሉት በኢትዮጵያ ውስጥ በቡና ስራዎች ላይ ተሰማርተው ያሉ ባለሙያዎች ስለ ቡና በቂ እውቀት እንደሌላቸው ይህም የስርዓተ ትምህርቱ ችግር ነው ብለዋል፡፡
“ሀገሪቱ ከውጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ውስጥ ትልቁ ድርሻ ቡና ሆኖ ሳለ ግን በዩንቨርሲቲዎች ስለ ቡና የሚሰጠው ትምህርት ከአንድ ኮርስ ያልበለጠ ነው ይህ መሆኑ ያሳዝናል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቡና አምራች አርሶ አደሮች ስለ ቡና ስራ እየተማሩ ያሉት አንድ ኮርስ ብቻ በወሰዱ የሰብል ሙያተኞች ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዚህ ምክንያት የኢትዮጵያ ቡና ስራ በተለምዶ እና ኋላ ቀር በሆኑ አሰራሮች እንዲመራ እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡
ይህን ችግር ለመፍታትም በቡና ምርት፣ ሽያጭ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም መወሰናቸውን ሁሴን አምቦ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ “ይርጋጨፌ ቡና ኢንስቲትዩት” በሚል ስያሜ እንደሚቋቋም የተገለጸ ሲሆን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚፈጅም ተገልጿል፡፡
በጌዴኦ ዞን በይርጋ ጨፌ እንደሚቋቋም የተገለጸው ይህ ኢንስቲትዩት በዲላ ዩንቨርሲቲ ስር እንደሚሆን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የኢንስቲትዩቱን ወጪ ቡና አምራቾች እና ላኪዎች በሚያዋጡት ገንዘብ እንደሚሸፈን የተገለጸ ሲሆን በዚህ ዓመት ግንባታው እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቡና በምታገኘው ጥቅም ልክ ምርቱ በሰለጠነ የሰው ሀይል እንዲመራ የሚያደርግ ስርዓት እንዳልዘረጋች ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የአውሮፓ ህብረት አካባቢ ጥበቃ ሕግ የኢትዮጵያን ቡና ገበያ ምን ያህል ይጎዳል?
ዘግይተንም ቢሆን በቡና ሽያጭ፣ ምርት እና ጣዕም ማሻሻል ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን መስጠት ጀምረናል፣ አሁን ላይ በሁለተኛ ድግሪ የቡና ባለሙያዎችን እያስተማርን ነው ብለዋ፡፡
በዲላ ዩንቨርሲቲ ስር ሆኖ ይቋቋማል የተባለው የይርጋለም ቡና ኢንስቲትዩት ሙሉ ትኩረቱን በቡና ምርት፣ንግድ፣ ጣዕም ማሻሻል እና ተያያዥ ችግሮች በሚፈቱበት መንገድ ላይ ያደርጋል ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ ሲሶው ወይም 33 ሚሊዮን ህዝብ በቡና እና ተያያዥ ስራዎች የሚተዳደር ሲሆን ከ5 ሚሊዮን በላይ ያህሉ ደግሞ የቡና ገበሬዎች ናቸው፡፡