ቡና ለመጫን ወደ ቴፒ ከተማ ያመሩ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውን አሽከርካሪዎች ተናገሩ
ለአንድ ወር ገደማ እንዳይንቀሳቀሱ የተደረጉት ተሽከርካሪዎቹ ከምርት ገበያ ቡና ለሀገር ውስጥ ገበያ የጫኑ ናቸው
የቡና እና ሻይ ባለ ስልጣን በበኩሉ ተሽከርካሪዎቹ የታገዱት ለውጭ ገበያ መቅረብ የነበረበትን ቡና ለሀገር ውስጥ ለማቅረብ ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ነው ብሏል
ቡና ለመጫን ወደ ቴፒ ከተማ ያመሩ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸውን አሽከርካሪዎች ተናገሩ፡፡
ከ25 ቀናት በፊት ቡና ለመጫን ወደ ደቡብ ምዕራብ ክልል ቴፒ ከተማ ያመሩ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ መታገዳቸው ተሰምቷል፡፡
ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ አሽከርካሪ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳለው ቡና ለመጫን ወደ ቴፒ ከተማ ከመጣ 25 ቀኑ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ቡናውን ቴፒ ከተማ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዝን ከጫንኩ በኋላ ተሽከርካሪውን ከግቢው እንዳላስወጣ ተነገረኝ የሚለው አሽከርካሪው ምክንያቱ እስካሁን ይህ ነው ብሎ የነገረኝ አካል የለም ብሏል፡፡
ላለፉት 25 ቀናት ከመኪናዬ ተለይቼ ሆቴል ውስጥ ነው ያለሁት የሚለው አሽከርካሪው በቶሎ ምላሽ ባለመሰጠቱ ምክንያት ላልተፈለገ ወጪ እና እንግልት መዳረጉን ተናግሯል፡፡
በሀገር ውስጥ የቡና ንግድ ስራ የተሰማሩት እና የገዙት ቡና እንዳይንቀሳቀስ ከታገደባቸው ነጋዴዎች መካከል አንዱ የሆኑት ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በህጋዊ መንገድ ከቴፒ ምርት ገበያ የገዛሁት ቡና ታግዶብኛል ብለዋል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት እኝህ ቡና ነጋዴ ቡናው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቴፒ ቅርንጫፍ አማካኝነት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ቡና ከሌላ ቡና አምራች መግዛታቸውን እና ተገቢውን ክፍያ መፈጸማቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከእኔ ጋር እኩል በተመሳሳይ ጊዜ እና ቦታ ቡና የገዙ ሌሎች ነጋዴዎች ለተወሰኑ ቀናት ከታገዱ በኋላ ቡናውን እንዲያጓጉዙ እንደተፈቀደላቸውም ገልጸዋል፡፡
“በአጠቃላይ የእኔን ጨምሮ 25 ተሽከርካሪዎች ከቴፒ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መጋዝን የጫኑትን ቡና እንዳያንቀሳቅሱ ከታገዱት ውስጥ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ 13ቱ ተሽከርካሪዎች ተለይተው ቡናቸውን እንዲያጓጉዙ ተፈቅዶላቸዋል” ሲሉም እኝህ ነጋዴ ነግረውናል፡፡
በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመጋዝን እና ጥራት ምርት ሃለፊ አቶ ሐብታሙ መኮንን በበኩላቸው ተቋሙ ካሉት 13 የምርት መሰብሰቢያ እና መገበያያ ማዕከላት ውስጥ በሰባቱ ለይ መስተጓጎል እንደገጠመ ተናግረዋል፡፡
ከነዚህ መካከል ቴፒ መጋዝን አንዱ ነው ያሉት አቶ ሐብታሙ ተሽከርካሪዎች ችግር ያጋጠማቸው የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከግንቦት 16 ጀምሮ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ያለበት ቡና ለሀገር ውስጥ ገበያ እየቀረበ ነው በሚል እግድ እንዲፈጸም ደብዳቤ በመጻፉ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ባለስልጣኑ በቴፒ፣ ቦንጋ፣ ጅማ፣ መቱ፣ ሚዛን አማን፣ጎደሬ፣ መንገሽ እና ጊምቢ ቅንጫፎች ግብይት የሚፈጸምባቸው የቡና ምርቶች የገበያ መዳረሻቸው ላይ ተጨማሪ ማጣራት ሳይደረግባቸው እንዳይንቀሳቀሱ እንዲደረግ ጠይቋል ተብሏል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ክልል ስር ያሉ የቡና ግብይት የሚፈጸምባቸው የምርት ገበያ ማዕከላት ላይ አጋጥሞ ከነበረው መስተጓጎል ውስጥ ከቴፒ ውጪ የሌሎቹ መፈታቱን የሚናገሩት አቶ ሐብታሙ በቴፒ ግብይት የተፈጸመባቸው 1 ሺህ 863 ኬሻ አጋጥሞ የነበረው ችግር በውይይት እንዲፈታ ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም በቴፒ መጋዝን ውስጥ ያለው ነገር ግን ያልተሸጠ 2 ሺህ 700 ኬሻ ቡና በተቀመጠው አሰራር መሰረት ቡናው ለውጭ ገበያ ነው ወይስ ለሀገር ውስጥ ገበያ መቅረብ ያለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ምርት ገበያው እና ባለ ስልጣኑ በጋራ ለማጣራት እና መፍትሄ እንዲሰጥ ከስምምነት ላይ መደረሱንም አቶ ሐብታሙ አክለዋል፡፡
በቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር በበኩላቸው ከቴፒ የምርት ገበያ ቅርንጫፍ እንዳይወጡ የተደረጉት ቡና የጫኑ ተሽከርካሪዎች ለውጭ ገበያ መዋል የነበረበትን ገበያ ለሀገር ውስጥ ገበያ ለማቅረብ ሲሞክሩ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታት ቡናን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ ናት ያሉት አቶ ሻፊ ነጋዴዎች ቡናውን ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ወደ ውጪ መላኳን ገለጸች
የሀገር ውስጥ ቡና ነጋዴዎች ሆን ብለው ቡናው የጥራት ችግር አለበት እንዲባል በአፈር በማሸት እና በመዘፍዘፍ የጥራት ጉድለት ያለበት ነው እንዲባል እና ለሀገር ውስጥገበያዎች እያቀረቡ ሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ እያሳጡ ነውም ብለዋል አቶ ሻፊ፡፡
በቴፒ ከተማ እንዳይንቀሳቀሱ የታገዱ ቡና የጫኑ ተሽከርካሪዎችም እየተጣራ ነው የተወሰኑትን አጣርተን ለቀናል በቀሪዎቹ ለይም የማጣራት ስራ እየሰራን ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ እየተጠናቀቀ ባለው የ2016 በጀት ዓመት ባለፉት 10 ወራት ውስጥ 260 ቶን ቡና ወደ ውጭ የላከች ሲሆን 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን ባለስልጣኑ አስታውቋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ካለባት ቡና ምርት ውስጥ 34 በመቶው ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚቀርብ ሲሆን የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑ ወደ ውጭ ለተላከው ቡና መጠን ማነስ ዋነኛው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡