መከላከያ በድሮን ጥቃት ንጹሃን ተገድለዋል የሚለውን ክስ አስተባበለ
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ “ታጥቆና ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ፀረ ሰላም ኃይልን ለይተን እንጂ ህዝብን በድሮን አንመታም” ብለዋል
ኢሰመኮ እና አለማቀፍ ተቋማት ግን ንጹሃን በድሮን ጥቃት መገደላቸውን መግለጻቸው ይታወሳል
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃን ተገድለዋል በሚል የሚቀርቡ ክሶችን አስተባበለ።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያው (ኢቲቪ) ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው “በድሮን ህዝብ መተን አናውቅም” ሲሉ የተደመጡት።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እየተካሄዱ ስላሉት ወታደራዊ ግጭቶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፥ “የኛ ድሮን ሸኔ ላይ ወይም ጃዊሳ ላይ ነው የሚያርፈው፤ እንጂ ህዝብ ላይ አያርፍም፤ ይህንምም ህዝቡ ያውቃል” ብለዋል።
ታጣቂ ሃይሎች ከህዝብ ጋር ሲቀላቀሉም የድሮን ጥቃት ከመፈጸም መቆጠባቸውን በመጥቀስ፥ “እንደዛማ ባይሆን ኖሮ እስካሁን አይቆዩም ነበር” ሲሉ አብራርተዋል።
“የምንዋጋው ለህዝባችን ነው” ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ፥ የመንግስት ፍላጎት ታጣቂዎችን ለይቶ በመምታት ማዳከምና ወደ ተራ ሽፍትነት ማውረድ ከዚያም ህዝቡ ራሱ እንዲዋጋቸው ማድረግ ነው ብለዋል።
በድሮን ጥቃት “ንጹሃን ተገደሉ፤ ተጨፈጨፉ” የሚሉ ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩትም “ህዝብን ምሽግ አድርገው ስልጣን ለማግኘት የሚሞክሩ ታጣቂዎች” ናቸው ሲሉም ከሰዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ይህን ይበሉ እንጂ መንግስታዊውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ን ጨምሮ የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማትና የመገናኛ ብዙሃን በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚወሰዱ እርምጃዎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ሲጠቅሱ ቆይተዋል።
ኢሰመኮ በአማራ ክልሉ ግጭት መንግስት ድሮኖችን በስፋት እየተጠቀመ መሆኑን መግለጹና እስካሁን በጥቂቱ 81 ንጹሃን በድሮን ጥቃት እና ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መንገድ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ማሳወቁ አይዘነጋም።
ከአንድ ወር በፊትም በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ሳሲት በተባለች ከተማ አቅራቢያ በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በጥቂቱ የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል።
መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ጀኔቫ ያደረገው የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በጥቅምት ወር 2016 በወደራ ወረዳ ባለ አንደኛ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ሶስት መምህራንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸው መግለጹ አይዘነጋም።
በምዕራብ ጎጃም ዋበር መናኸሪያ ትራንስፖርት እየጠበቁ በነበሩ ንጹሀን ላይ በተፈጸመ ተመሳሳይ የድሮን ጥቃት 13 ንጹሀን ዜጎች እንደተገደሉ በመጥቀስም መንግስት አለማቀፍ የዜጎች ሰብአዊ መብትን ከሚጥስ ድርጊት እንዲቆጠብ ጠይቆ ነበር።
በደብረ ማርቆስ፣ በመራዊ፣ በሰሜን ሸዋ በረኸት ወረዳ፣ በደቡብ ወሎ ዞን ወገል ጤና ከተማ እና ሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች የተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እና ከህግ አግባብ ውጪ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች በርካቶችን ለህልፈት መዳረጋቸው ሲነገር ቆይቷል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ግን የሚቀርበውን ክስ መሰረተ ቢስ እና ታጣቂዎች “ህዝብን ምሽግ አድርገው ስልጣን ለመያዝ” የሚያደርጉት ትግል አካል አድርገው አቅርበውታል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ በአማራ ክልል የድሮን ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑን በታህሳስ ወር መጀመሪያ በይፋ ማረጋገጣቸው ይታወሳል።