“በአማራ ክልል የድሮን ጥቃት” እንደሚቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ተናገሩ
ኢታማዦር ሹሙ “የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት እንደ ነፍስ አድን የማያዩ ስድ አደግ፣ ንቅል እና ቅጥረኞች ናቸው” ብለዋል
ከውጭ ሀገራት ሰራዊት አሰልጥኑልን እና ጎብኙን ጥያቄዎች መብዛታቸውን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል
በአማራ ክልል የድሮን ጥቃት እንደሚቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ተናገሩ፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ቃለመጠይቅ አድርገዋል፡፡
ኢታማዦር ሹሙ በዚህ ቃለ መጠይቃቸው በአማራ ክልል ስላለው ጦርነት፣ ስለ ሀገር መከላከያ፣ ስለ ታንዛኒያው ድርድር፣ ስለ አልሻባብ እና ሌሎች የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቃለ መጠይቁ ወቅት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል እንዱ የሆነው የኢትዮጵያ አሁናዊ ሰላም ምን ይመስላል? የሚለው ሲሆን ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ በምላሻቸውም ሰሜን እዝ ከተመታ በኋላ ከባድ ጦርነት ለሁለት ዓመት መደረጉን፣ ሸኔ ይህን ግርግር ለመጠቀም ብዙ ጥረት ማድረጉን፣ በጋምቤላ፣ አማራ ክልል የተወሰነ ቦታ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል ምዕራብ ኦሮሚያ ከባድ የጸጥታ ችግር ነበር ብለዋል፡፡
"አሁን ላይ የኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር በብዙ መልኩ ተሸሽሏል" ያሉት ኢታማዦር ሹሙ "የአማራ ክልልን የሽፍታ መፈንጫ ለማድረግ የሞከረው ጽንፈኛ ሀይል ተመቶ ወደ ጫካ እና በረሃ ለመግባት ተገዷል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ አጠቃላይ የጸጥታው ሁኔታ አሁን ላይ ተቀይሯል ያሉት ኢታማዦር ሹሙ በኦሮሚያ ክልል የነበረው ችግር ተመሳሳይ እንደነበር እና መንግስትን በማስጨነቅ ተገዶ ወደ ድርድር እንዲገባ ለማድረግ ይደረግ የነበረው ጥረት አለመሳካቱንም ገልጸዋል፡፡
የፓስፖርት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በአንጻራዊነት መቀነሱ ተገለጸ
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ በኦሮሚያ ክልል በሸኔ ለብዙ ዓመት ሲሰለጥን የነበረው ዋና ሀይል በሀገር መከላከያ መመታቱንም ተናግረዋል።
ሌላኛው የጦር ሀይሎች አዛዡ በቃለ መጠይቃቸው ላይ ያነሱት ጉዳይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወቅታዊ አቋም ሲሆን ሰራዊቱ አሁንም መደበኛ ተልዕኮውን እየተወጣ ሀገርን በማዳን ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ እና ሀገሩን የሚወድ ቢሆንም ጥቂት ህዝቦች ግን ለስልጣን ተኝተው የማያድሩ፣ በቀላሉ ለውጭ ሀይሎች የሚገዙ ናቸው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡
"የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት እንደ ነፍስ አድን የማያዩ ስድ አደግ ናቸው፣ ንቅል ናቸው ቅጥረኞች ናቸው" ሲሉም ኢታማዦሩ ሹሙ በቃለ መጠይቁ ላይ አንስተዋል።
"የእኛ ሰራዊት አፍሪካ በሙሉ ፣በአረብ ሀገር እና በመላው ዓለም ተፈላጊ ሰራዊት ነው እንዴት ነው እምታሰለጥኗቸው እያሉ ይጠይቁናል"ም ብለዋል፡፡
በአማራ ክልል ያለውን ሁኔታም ሲገልጹ "አማራ ክልል ህዝቡ ለሰራዊቱ እያደገው ያለው ድጋፍ ከፍተኛ ነው፣ ሰራዊታችን በሌለበት አካባቢ ያሉ ህዝቦች በሌሊት እየመጡ ለእኛም አካባቢ መከላከያ ሰራዊት መድቡልን እያሉ ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው ሀቅ ይህ ነው፡፡" ብለዋል ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ።
እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ የጥትቅ ትግል ማድረግ የሚያስችል እና ላይታረቅ የሚችል እንደሌሉ የተናገሩት አዛዡ ጥያቄዎች ሁሉ በድርድር ሊፈቱ የሚችሉ እና በአማራ ክልልም ያለው እንደ ህገመንግስት ይሻሻል፣ የወሰን ጥያቄ ወደ ትጥቅ ትግል ሊያስገባ የሚችል አይደሉም ብለዋል።
"በአማራ ክልል ያለው ጥያቄ እየተገደልን ነው እየተፈናቀልን ነው የሚል ነው፣ ላለመገደል አለመግደል ነው፣ ማን ነው ግድያ የጀመረው? እየተገደልን ነው ለሚለው ጥያቄ ላለመገደል አለመግደል ነው፣ ከገደልክ በኋላ ስትገደል መቀበል ነው” ብለዋል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ አክለውም በአማራ ክልል የነበረው መከላከያ ሰራዊት ሬጅመንቶች እንደ ሰሜን እዝ ባይሆንም የነበረው ሀይል ተመቷል ይህ ስህተት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ፋኖ ጋር ጸብ የለንም ያሉት ዋና አዛዡ በክልሉ የተከሰተው ግጭት እንዲፈጠር አልፈለግንም ነበር፣ ባለፉት ወራት በፍጥነት ክልሉን ወደቀድሞ ሁኔታው ሙሉ ለሙሉ መመለስ ያልተቻለው በህዝብ ላይ የከፋ ጉዳት ላለማድረስ ህዝቡን እና ጽንፈኞችን አብሮ ላለመምታት በሚል በተወሰደ ጥንቃቄ መሆኑንም ተናግረዋል ።
በአማራ ክልል እየተፈጸሙ ባሉ የድሮን ጥቃቶች ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ "ድሮን የተሰራው ለውጊያ ነው፣ የገዛነው ልንዋጋበት ነው፣ ድሮንም ልክ እንደክላሽ የራሱ አላማ አለው፡፡ ድሮንን የምንጠቀመው የጠላትን ጠንካራ ብልት ለመምታት ነው፡፡ ህዝብ ላይ የድሮን ጥቃት አናደርስም፡፡ እስካሁን ባለን አቅም ልክ ድሮንን አልተጠቀምንም ምርጥ ኢላማ ስናገኝ ህዝቡን በማይጎዳ መልኩ እንመታለን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
"የድሮን ጥቃቱ ይቀጥላል" ያሉት የጦር ሀይሎች ዋና አዛዥ ብዙ ኢላማዎችን ህዝብ እንዳይጎዳ በሚል የተውናቸው አሉ" ብለዋል።
ዋና አዛዡ አክለውም አልሻባብ ለኢትዮጵያ ስጋት እንደማይሆን የሰራቂቱ ቀጣይ ትኩረት የኢትዮጵያ ህዝብ እያደገ በመሆኑ እና ይህንን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂ ማዘመን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጋር መስራት የሚፈልጉ የውጭ ሀገራት እየጨመሩ እንደመጡ የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ አብረን እንስራ የሚሉ እና ጎብኙን የሚሉ ጥያቄዎች እንደበዛባቸውም ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ካምፑ ይመለስ በሚል የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍን መንግሥት መከልከሉ ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነም ተገልጿል።
በከተሞች የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በውጊያ የተመታው ጽንፈኛ ሀይልን ወደ ከተማ እንዲገባ ለማድረግ ስለመዘጋጀቱም የጦር ሀይሎች ዋና አዛዡ ጠቅሰዋል።
በአማራ ክልል የተለያዩ ቦታዎች ላይ በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በርካታ ንጹሀን ዜጎች ስለመገደላቸው እና የህዝብ መገልገያ ተቋማት እንደተጎዱ ተመድን ጨምሮ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በሪፖርቶቻቸው ላይ ጠቅሰዋል።