በሰሜን ሸዋ ዞን በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በጥቂቱ 30 ንጹሃን ተገድለዋል- ነዋሪዎች
በዞኑ ሳሲት በተባለች ከተማ ህዝብ ያሳፈረ አይሱዙ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመው ጥቃት 18 ሰዎች መቁሰላቸውም ነው የተገለጸው
የኢትዮጵያ መንግስት በታጣቂ ሃይሎች ላይ የድሮን ጥቃት መፈጸም እንደሚቀጥል መግለጹ ይታወሳል
በአማራ ክልል በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በጥቂቱ 30 ንጹሃን መገደላቸው ተነገረ።
በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ሳሲት በተባለችው ከተማ አቅራቢያ 50 ሰዎችን ያሳፈረ አይሱዙ ተሽከርካሪ መንገደኞችን ለማውረድ በቆመበት ተፈጽሟል በተባለው ጥቃት 18 ሰዎች መቁሰላቸውንም ነው የአይን እማኞችን የጠቀሰው የሪሊፍ ዌብ ዘገባ የሚያሳየው።
የድሮን ጥቃቱ ሲፈጸም በአካባቢው በመከላከያ ሰራዊትና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት እንዳልነበር የተናገሩት ነዋሪዎች፥ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላም ድሮኖች በአካባቢው ሲሽከርከሩ እንደነበር ገልጸዋል።
ሬውተርስ በበኩሉ ባለፈው ሰኞ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት በጥቂቱ 15 ንጹሃን ህይወት ማለፉንና ጥቃቱ መከላከያና የፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ ከሚያደርጉበት አካባቢ በ24 ኪሎሜትር ርቀት ላይ መፈጸሙን ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
“መጀመሪያ ከባድ ፍንዳታ ሰማን ከዚያም አካባቢው በጭስ እና አቧራ ተሸፈነ፤ የ15 ሰዎችን አስከሬን ሰብስበናል፤ እጅና እግራቸው እዚያም እዚህም የተበታተኑ ሟቾችን አስከሬን መሰብሰብ ዘግናኝ ነበር” ብለዋል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ቄስ ለሬውተርስ በሰጡት ቃል።
በጥቃቱ 10 የቤተሰብ አባላቱን እንዳጣ የሚገልጽ ሌላ የሳሲት ነዋሪም በጥቃቱ ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውንና ከባድ ፍንዳታ ከመሰማቱ በፊት ትንሽ ድሮን መመልከቱን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአማራ ክልሉ ግጭት ድሮኖችን በስፋት እየተጠቀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል።
ኮሚሽኑ እስካሁን በጥቂቱ 81 ንጹሃን በድሮን ጥቃት እና ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መንገድ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው መግለጹም አይዘነጋም።
በሰብአዊ መብት ኮሚሽን የቀረቡትን የተወሰኑ ክሶች ውድቅ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት፥ በአማራ ክልል ህግና ስርአትን ለማስከበር እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበኩላቸው በክልሉ በሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ዙሪያ ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ለቀረበላቸው ጥያቄ “ህዝብ ላይ የድሮን ጥቃት አንፈጽምም” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
“ድሮን የገዛነው ልንዋጋበት ነው፤ እስካሁን ባለን አቅም ልክ ድሮንን አልተጠቀምንም ምርጥ ኢላማ ስናገኝ ህዝቡን በማይጎዳ መልኩ እንመታለን” ሲሉም በክልሉ የድሮን ጥቃቱ እንደሚቀጥል ማብራሪያ መስጠታቸው አይዘነጋም።