በአማራ ክልል በተፈጸመ የድሮን ጥቃት መምህራንን ጨምሮ ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን ተመድ ገለጸ
ተመድ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ንጹሀንን ከማንኛውም ጥቃት እንዲጠብቁ አሳስቧል
የፋኖ ታጣቂዎች የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ 21 ሰዎችን ገድለዋልም ተብሏል
በአማራ ክልል በተፈጸመ የድሮን ጥቃት መምህራንን ጨምሮ ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን ተመድ ገለጸ።
ዋና መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ጀኔቭ ያደረገው የተመድ ሰብዓዊ መብት ቢሮ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዳሳሰበው አስታውቋል።
ቢሮው በመግለጫው በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ንጹሀን ዜጎች የከፋ ጉዳት እያስተናገዱ መሆኑን አስታውቋል።
በአማራ እና ሌሎች ክልሎች የጅምላ እስር እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው ያለው ቢሮው ጉዳዩ እንዳሳሰበው ገልጿል።
በአማራ ክልል በፈረንጆች ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ. ም ወደራ ወረዳ ባለ አንደኛ ትምህርት ቤት ላይ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በፈጸመው የድሮን ጥቃት ሶስት መምህራንን ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።
እንዲሁም ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም ምዕራብ ጎጃም ዋበር መናኸሪያ ትራንስፖርት እየጠበቁ በነበሩ ንጹሀን ላይ በተፈጸመ ተመሳሳይ የድሮን ጥቃት 13 ንጹሀን ዜጎች እንደተገደሉም ቢሮው በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።
እነዚህ የድሮን ጥቃቶች ዓለም አቀፍ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ በመሆኑ ጥቃቱ እንዲቆም ቢሮው ጠይቋል።
በማዕከላዊ ጎንደር ጯሂት ከተማ የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች በመኖሪያ ቤቶች ላይ በባደረሱት ጥቃት ስድስት ንጹሀን ዜጎች ሲገደሉ 14 ሰዎች ደግሞ እንደቆሰሉ ተገልጿል።
የፋኖ ታጣቂዎችም በደቡብ ጎንደር አለም በር ባደረሱት ተመሳሳይ ጥቃት የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ 21 ሰዎች እንደተገደሉም የተመድ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ቢሮ አስታውቋል።
እየተካሄዱ ያሉ የመብት ጥሰቶች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የሽግግር ፍትህ ስርዓትን እንዳይሳካ ሊያደርግ እንደሚችልም ቢሮው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
የሰብዓዊ መብት ቢሮው አክሉም ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ንጹሀንን ከማንኛውም አደጋ የመጠበቅ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከሁለት ሳምንት በፊት በክልሉ እየተፈጸሙ ስላሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተመሳሳይ ሪፖርት ያወጣ ቢሆንም መንግሥት የኢሰመኮን ሪፖርት ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከዚህ ቀደም ባወጣው ሪፖርቱ፤ በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር/ድሮን ድብደባ ጭምር የታገዘ ነው ያለ ሲሆን በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን አመላክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ዙሪያ በሰጠው ምለሽ፤ የኢሰመኮ ሪፖርት የመንግሥትን እንቅስቃሴ ዐውድ ከግምት ያላስገባ፣ በበቂ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ እና ከእውነታ ያፈነገጠ መሆኑን መግለጹ አይዘነጋም።
መንግሥት በአማራ ክልል ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት እና የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ለማረጋገጥ ጥንቃቄ የተሞላባቸው እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንም አረጋግጧል።
የመንግሥት አክሎም የአማራ ክልል ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን እና በክልሉ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መታደግ እንደተቻለ ገልጿል።