ባንኮች አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን እስከ 125 ብር እየመነዘሩ ነው
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ዶላር በ108 ብር እየገዛ፤ በ119 እየሸጠ ይገኛል
የጳጉሜ 4 የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ምን ይመስላል?
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አመት መቃረቡን ተከትሎ ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ እየጠየቁ ነው።
ዲያስፖራው በህገወጡ (ጥቁር ገበያ) ከመላክ ይልቅ ህጋዊውን መንገድ እንዲመርጥ የሚያበረታታ ተመንም እያወጡ ሲሆን፤ ባንኮች በማህራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት የጳጉሜ 4 2016 የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ላይ የዋጋ ልዩነት ታይቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ጳጉሜ 4 2016 የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ ዶላር መግዣ ዋጋን ቅዳሜ ሲገዛበት በነበረበት ዋጋ ማለትም 1 ዶላርን በ108.0728 ብር እየገዛ ይገኛል። መሸጫው ላይም ጭማሪ ሳያደርግ 119.9068 ብር እየገዛ ይገኛል።
የእንግሊዝ ፓውንድ በ135.5141 ብር እየገዛ በ151.1231 ብር እንደሚሸጥም አስታውቋል።
ንብ ባንክ መስከረም 30 2017 የሚቆይ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ በዚህም እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚላከውን የውጭ ሀገር ገንዘብ አንዱን የአሜሪካ ዶላር በብር 125 ምንዛሪ እንደሚያስረክብ አስታውቋል።
ንብ ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገው መደበኛው የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ107.8729 ብር እየገዛ በ120.8176 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።
ኦሮሚያ ኮኦፕሬቲቭ ባንክም በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የምንዛሬ ዋጋ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን እስከ 125 ብር እንደሚመነዝረ አስታውቋል።
ኦሮሚያ ኮኦፕሬቲቭ ባንክ በመደበኛ የምንዛሬ ዋጋው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ107.8507 ብር እየገዛ በ118.6357 ብር እየሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን አስታውቋል።
አቢሲኒያ ባንክም ዕለታዊ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከውጪ በሃዋለ የተላከ አንድ የአሜሪካ ዶላርን ከእለታዊ ተመን በተጨማሪ 16% ጉርሻ እንደሚሰጥ እና በዚህም 1 ዶላርን እስከ 125 ብር እንደሚመነዝረ አስታውቋል።
አቢሲኒያ ባንክ በመደበኛ የምንዛሬ ዋጋው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ108.0729 ብር እየገዛ በ121.0416 ብር እየሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን አስታውቋል።