ጠ/ሚ አብይ በፓርላማ ንግግራቸው ስለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ምን አሉ?
በተለያዩ ዘርፎች እድገቶች እየተመዘገቡ ቢሆንም “ለሺ አመት በድህነት የቆየች ሀገርን በ10 አመት ልንቀይራት አንችልም” ብለዋል
የሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርትና የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ በእጥፍ መጨመሩን አብራርተዋል
የኢትዮጵያ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 164 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
የሀገሪቱ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢም ከአምስት አመት በፊት ከነበረበት 882 ዶላር ወደ 1549 ዶላር ከፍ ማለቱን ነው ለህዝብ እንደራሴዎች ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ የተናገሩት።
ጦርነት፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የአለም የንግድ መዛባት ያስከተለው ጫና ቢኖርም በአምስት አመት ውስጥ ኢትዮጵያ ፈጣን እድገት እያስመዘገበች እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የጂዲፒ እና የነፍስ ወከፍ ገቢ እድገቱ የእያንዳንዱን ቤተሰብ ችግር እና የኑሮ ውድነት ፈተና መፍታት አልቻለም።
“ለሺ አመት በድህነት የቆየች ሀገር በ10 አመት ልንቀይራት አንችልም መሰረት ነው የምንጥለው፤ የኢትዮጵያ ችግር በቀላሉ የሚፋቅ አይደለም” ይላሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ።
በቀጣይ አምስት እና አስር አመታት የኑሮ ውድነት፣ የውጭ ምንዛሬ እና ሌሎች ችግሮች እየተነሱ መቀጠላቸው አይቀሬ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፍ የተመዘገቡ እድገቶችንም አንስተዋል።
22 ሄክታር መሬት በማረስ 800 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ የተሰራው ስራ አበረታች ውጤት እየታየበት መምጣቱን ያነሱት ዶክተር አብይ፥ የግብርናው ዘርፍ የ6 ነጥብ 3 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን አብራርተዋል።
የኢንዱስትሪ ዘርፉም የ6 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንና የፋብርካዎችን የማምረት አቅም ወደ 55 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል።
ለሀገር ውስጥ ፍላጎት የሚሆኑ ምርቶችን በማምረት ረገድም ምርታማነትን በ8 በመቶ ማሳደግ መቻሉን በመጥቀስ የድንጋይ ከሰልና የቢራ ገብስ ማስገባት መቆሙን አውስተዋል።
የመንግስት ገቢን ለማሳደግ በተከናወኑ ስራዎችም በ2011ከነበረበት 235 ቢሊየን ብር በ2015 ወደ 407 ቢሊየን ብር ማሳደግ መቻሉን ነው የጠቀሱት።
በዚህ አመት 520 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በዚህ ሩብ አመት ከ100 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉንም በማንሳት።
ወጪ ግን ጭማሪ እያሳየ ነው፤ ባለፉት ሶስት ወራት ወጪ የተደረገው 141 ቢሊየን ዶላር ከአምናው የ20 በመቶ እድገት ያሳየ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ።
ኢትዮጵያ በ2016 25 ቢሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ማቀዷንም አብራርተዋል።