“የታጠቁ ሃይሎች መንግስትን ማሸነፍ አይችሉም “- ጠ/ሚ አብይ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ እንደራሴዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፥ መንግስት አቅዶ የጀመረው አንዳችም ጦርነት የለም ሲሉ ተደምጠዋል
መንግስት ለሰላማዊ አማራጮች በሩ ክፍት መሆኑንም ገልጸዋል
በወቅታዊው የአለም ሁኔታም ሆነ በኢትዮጵያ የታጠቁ ሃይሎች መንግስትን አሸንፈው መጣል እንደማይችሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ እንደራሴዎች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በትጥቅ ትግል መንግስት ማሸነፍ ከባድ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት “ለካፒታል ፕሮጀክቶች የሚመድበውን 10 ቢሊየን ዶላር ለጦር መሳሪያ መግዣ ሊያውለው ይችላል፤ ለታጠቁ ሃይሎች ግን 10 ቢሊየን ዶላር መርዳት ቀርቶ ማበደር የሚፈልግ አንድም መንግስት የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በክላሽ መንግስት መገልበጥ ከባድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
“በዶላር ከመገዳደል በሃሳብ መገዳደር ይሻላል” ያሉት ዶክተር አብይ፥ የሃገር ኢኮኖሚን ክፉኛ የሚጎዳን ጦርነት ማስቆም ተገቢ ስለመሆኑም አብራርተዋል።
በተለያየ ቦታ ክላሽ አንግበው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሰላም ዋጋ ሰጥተው በድርድር ልዩነትን ለመፍታት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ በማቅረብ መንግስታቸውም ለዚህ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል።
“አማራና ኦሮሞ በሰላም ለመኖር ያላቸው ምርጫ አንድ ብቻ ነው፤ ተከባብሮና አብሮ መኖር ውጭ አማራጭ የላቸውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ መንግስት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል አቅዶ የጀመረው ጦርነት እንደሌለም አንስተዋል።
በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የታጠቁ ሃይሎች ጠመንጃቸውን አውርደው ለንግግር እንዲዘጋጁም ነው የጠየቁት።
በአማራ ክልል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንጻራዉ ሰላም ማምጣቱንና የክልሉን መንግስት ከመፍረስ መታደጉን በመጥቀስም በክልሉ የተሟላ ሰላም ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
የፌደራል መንግስት በትግራይና አማራ ክልሎች አወዛጋቢ የሆኑ የወሰን ጉዳዮች በህዘበ ውሳኔ እንዲፈታ ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፥ ለዚህም ከሁለቱም ክልሎች አመራሮች እና ህዝቦች ጋር ውይይት መደረጉን ጠቅሰዋል።
“የህዝበ ውሳኔው ብቸኛ አማራጭ አይደለም፤ የሁለቱንም ክልሎች ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ፤ ህዝብ የሚያቀራርብ ሌላ መፍትሄ ካለ መጠቆምና መነጋገር ይቻላል” ሲሉም ተደምጠዋል።
መፍትሄ መጠቆም ሳይቻል በመንግስት የቀረበውን የመፍትሄ ሃሳብ አለመቀበል ግን ተገቢ አለመሆኑን ነው ያሳሰቡት።