ኤርትራዊያንን ጨምሮ ከ1 ሚሊዮን በላይ የሆኑ የ26 ሀገራት ስደተኞች በኢትዮጵያ ተጠለዋል ተብሏል
ኢትዮጵያ ኤርትራዊያን ስደተኞች እየተዋከቡ ነው መባሉን አስተባበለች።
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች በመንግሥት እየተዋከቡ ነው መባሉን የስደተኞችና ተመላሾች አግልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስተባብሏል፡፡
አገልግሎቱ በመግለጫው በኢትዮጵያ የተጠለሉ ኤርትራውያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ለእስርና እንግልት እየተዳረጉ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡
ከሰሞኑ እንደ በርካታ አለም አቀፍ ሚዲያዎችን ጨምሮ በስፋት የተዘገበው የኤርትራዊያን በአዲስ አበባ መዋከብ ከእውነታው የራቀ ነው በማት አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ በሚገኙ በኤርትራውያን ላይ የጅምላ እስራት እየተፈጸመባቸው መሆኑ ከሰሞኑ ሲዘገብ ነበር፡፡
ምንም እንኳን መሰል ክስተቶች አዲስ ባይሆኑም በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ የጅምላ እስራት ግን ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው ኤርትራውያን ከሰሞኑ ለቪኦኤ መናገራቸው ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የስደተኞችን ጉዳይ የሚከታተለው አገልግቱ በሰጠው ምላሽ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ያነጣጠረ የዘፈቀደ እስርና እንግልት እየተከናወነ ነው መባሉን መሰረተ ቢስ ብሎታል፡፡
ተቋሙ የሚዲያዎቹን ዘገባ ተከትሎ አደረኩት ባለው ማጣራት ሕጋዊ የስደተኝነት ዕውቅና ኖሯቸው ለእስርና እንግልት የተዳረጉ ስደተኞች አለመታሰራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ስደተኞች የሀገሪቱን ሕግና ሥርዓት ጥሰው ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ የሚኖር ከሆነ፣ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚከታተልም ጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ ከ26 ሀገራት ከለላና ጥበቃ ፈልገው ወደ ሀገሯ ለመጡ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላና ጥበቃ እየሰጠች መሆኗን ተቋሙ በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
በኢትዮጵያ ከተጠለሉ ስደተኞች ውስጥ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ከደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የመጡ ናቸው።