በነዳጅ የሚሰሩ የቤት መኪናዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተጣለው ክልከላ አልተነሳም
የገንዘብ ሚኒስቴር ለብሄራዊ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ በተወሰኑ እቃዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ገደብ መነሳቱን ጠቁሟል
ኢትዮጵያ 38 አይነት ምርቶች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ እገዳ ጥላ መቆየቷ ይታወሳል
በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተጣለው ክልከላ አለመነሳቱን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ በተወሰኑ እቃዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ገደብ መነሳቱን የሚጠቁም ደብዳቤ ለብሄራዊ ባንክ እና ጉምሩክ ኮሚሽን ጽፏል።
በዚህ ደብዳቤ ላይ የውጭ ምንዛሬ ገደቡ በነዳጅ በሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች እና ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) ላይ የተጣለው እገዳ እንዳልተነሳ ተመላክቷል።
ብሄራዊ ባንክ ትናንት ባወጣው መግለጫ ወደሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ 38 አይነት ምርቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ መነሳቱን ቢገልጽም የገንዘብ ሚኒስቴር በዛሬው እለት ለባንኩ በጻፈው ደብዳቤ በነዳጅ በሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ላይ የተጣለው እገዳ እንዳልተነሳ ገልጿል።
ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር 2014 ወደሀገሪቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይገቡ ከከለከለቻቸው 38 ምርቶች በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች መካተታቸው ይታወሳል።
ብሄራዊ ባንክ በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎችን ለማስገባት ለሚፈልጉ አስመጪዎች የባንክ መተማመኛ ሰነድ (LC) እንዳይከፈትላቸው ውሳኔ ማሳለፉም አይዘነጋም።
ለዚህም በዋናነት ተነስቶ የነበረው ምክንያት የአስመጪዎቹ የውጭ ምንዛሬ ዋነኛ ምንጭ የህገወጥ የምንዛሬ ገበያው እና ህገወጥ ሃዋላ በመሆኑ ክልከላው ህገወጥ የምንዛሬ ገበያውን ዝቅ ያደርገዋል የሚል ነበር።
ይሁን እንጂ ክልከላው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ ቢያደርግም በሁለት አመት ውስጥ ህገወጥ የምንዛሬ ገበያው ዝቅ እንዲል ማድረግ አለመቻሉን ባለሙያዎች ያነሳሉ።
ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ታግደው ከነበሩትና ከሀምሌ 21 2016 ጀምሮ እገዳው ከተነሳላቸው ምርቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦
- የተገጣጠሙ ሞተር ሳይክሎች (በኤሌክትሪክ ሞትር የሚሰሩ)
- ከረሜላዎች፣ ማስቲካዎች፣ ቸኮሌት፣ ብስኮቶች እንዲሁም ዋፈሮች
- የፍራፍሬ ጫማቂ እና የታሸጉ ፍራፍሬዎች እንዲሁም ከፍራፍሬ የተዘጋጁ ጃሶች እና የድንች ጥብሶች
- ውስኪ፣ ወይን፣ ቢራ እና ሌሎች የመጠጥ አልኮሎች እንዲሁም ሲጋራ
- የሰው (ሁማን) እና ሰው ሰራሽ ፀጉር (ዊግ)፣ የውበት መጠበቂያዎች፣ ሽቶ፣ ሳሙናዎች፣ እንዲሁም ቦርሳና ዋሌት
- የገበታ ጨው፣ የዶሮ ስጋ፣ የአሳማ ስጋ፣ ቱናዎች፣ ሰርዲኖች እና ሌሎች የአሳ ምርቶች
- የእጅ፣ የግድግዳ እና የጠረጴዛ ሰዓቶች፣ ዣንጥላዎች እና ምንጣፎች