ብሔራዊ ባንክ ከዛሬ ጀምሮ በገበያ ስለሚወሰነው የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አደረገ
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ያስገኛል ያላቸውን ጥቅሞችም ዘርዝሯል
የኢትዮጵያ መንግስት አደረኩት ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በትናንትናው እለት አስታውቋል
ብሔራዊ ባንክ ከዛሬ ጀምሮ በገበያ ስለሚወሰነው የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አደረገ።
የኢትዮጵያ መንግስት አደረኩት ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በትናንትናው እለት አስታውቋል።
ብሔራዊ ባንክ በዛሬው እለት ጠዋት በሰጠው መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ስለገለጸው በገበያ ወይም በፍላጎት እና አቅርቦት ላይ ስለሚመሰረተው የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ነገሮች ይፋ አድርጓል።
ባንኩ እንደገለጸው የውጭ ምንዛሬ ተመን በባንኮች እና በደንበኞች መካከል እንዲወሰን፣ የውጭ ምንዛሬ ወደ ብሔራዊ ባንክ ማስተላለፍ እንዲቀር፣ በ38 የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ ተጥሎ የነበረው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ገደብ እንዲነሳ፣ ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ነጋዴዎች ለራሳቸው የሚያስቀሩት የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከ40 ወደ 50 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪም ባንኮች ለተለያዩ ሸቀጦች የሚጠቀሙበት የውጭ ምንዛሬ አሰራር እና አደላደል እንዲቀር እንደሚደግ፣ የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች እንደሚቋቋሙ፣ ሸቀጦችን በፍራንኮ ቫሉታ ከማስገባት ጋር በተያያዘ የተጣሉ ክልከላዎች በቅርቡ እንደሚሻሻሉ፣ በሀዋላ ወይም በውጭ ምንዛሬ የሚከፈል ደሞዝ ያላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የውጭ ምንዛሬ አካውንቲ እንዲከፍቱ መፈቀዱን እና የግል ኩባንያዎች ወይም ባንኮች በሚወስዷቸው የውጭ ብድሮች ላይ ይከፍሉት የነበረው የወለድ ተመን ጣሪ እንዲነሳ መደረጉን ብሔራዊ ባንኩ ጠቅሷል።
ብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ ያስገኛል ያላቸውን ጥቅሞችም ዘርዝሯል።
በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበረው የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት አላማው የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ተመን እንዲኖር እና የዋጋ ንረት ዝቅ እንዲል ለማደረግ ቢሆንም፣ "በሂደት ግን ለጥቁር ገበያ መስፋፋት፣ ለከፍተኛ የዋጋ ንረት...." ምክንያት በመሆኑ ማሻሻያው አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብሏል ባንኩ።
የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኝ ስራ የተሰማሩ ሰዎችን መጥቀም፣ የውጭ ምንዛሬው በተገቢው መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ማድረግ፣ በሀገር ውስጥ የሚያመርቱ ኢንዱሰትሪዎች እንዲበረታቱ እና የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገር ውስጥ ኢንዲገቡ ማበረታታት እና ህጋዊ ያልሆኑ የውጭ ምንዛሬን ግብይትን ማስቀረት የማሻሻያው ዋና ዋና ጠሜታዎች ናቸው ብሏል ባንኩ።
መንግስት በውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ማሻሻያ ምክንያት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች እንዳይጎዱ ከውጭ በሚገቡ አንዳንድ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ድጎማ ለማድረግ መወሰኑን እና የበጀት ጉድለትን በማያባብስ መልኩ ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ መታሰቡን ባንኩ ገልጿል።
ባንኩ "የሽግግር ወቅት ወጪዎችንና የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ የሚያስከትላቸውን ጫናዎች ለመቀነስ የሚረዳ 10.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ትልቅ የገንዘብ ድጋፍ ከውጭ አጋሮች ተገኝቷል" ብሏል። ባንኩ እንዳለው ይህ "ድጋፍ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ ከዓለም ባንክና ከአበዳሪዎች የሚገኘውን" እንደማጨምር ባንኩ ገልጿል።
ነገርገን በሁለተዮሽ የማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ፣ በገንዘብ ልውውጥ የሚመጣውን 2.8 ቢሊዮን ዶላር፣ ከአለም ባንክ፣ ከአለምአቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን(አይኤፍ) እና ከሌሎች ባለብዙ ወገኖች ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውን እንደማይጨምር ጠቅሷል።
ባንኩ ከአለም የገንዘብ ድርድት (አይኤምኤፍ) እና የአለም ባንክ ድጋፍ የተገኘው መንግስት ሪፎርም በመስራቱ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ብድር ለማግኘት ከአይኤምኤፍ ጋር ለረጅም ጊዜ ድርድር ሲያደርግ የነበረት ጉዳይ ዋነኛው ጉዳይ የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲተመን ማድረግ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል።
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ስራዎች ወደ ባንኮች ስለላለፉ፣ ማሻሻያዎቹ መተግበራቸውን ለማረጋገጥ ክትትል እንደሚያደርግ ገልጿል።