ከኤሌክትሪክ ውጪ በነዳጅ የሚሰራ የቤት አውቶሞቢል ለማስገባት የሚሞክሩ አካላትን አላስተናድም- የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር
“አልሰማንም በሚል በነዳጅ የሚሰሩ አውቶሞቢሎች ገዝተው የሚመጡ አካላት አሉ” - ዶክተር አለሙ ስሜ
ኢትዮጵያ የቤት አውቶሞቢል የኤልክትሪክ ካልሆነ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መከልከሏ ይታወቃል
ከኤሌክትሪክ ውጪ በነዳጅ ለሚሰራ አዲስ የቤት አውቶሞቢል አገልግሎት እንደማይሰጥ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶክተር) በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው የመስሪያ ቤታቸውን የ6 ወር አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ዶ/ር አለሙ በማብራሪያቸው፤ “ማንኛውም የቤት አውቶሞቢል የኤሌክትሪክ ካልሆነ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ መንግስት ውሳኔ አስተላልፏል” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በስፋት እንደምታመርት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥ የኤሌክትሪክ ዋጋ ከነዳጅ አንጸር ሲታይ በጣም ርከሽ በመሆኑ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ተመራጭ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት አቀንቃኝ መሆኗን በመጥቀስም የአየር ንብረት ብክለትን ለመከላከል ረገድ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ተመራጭ መሆናቸውን ነው ያነሱት።
የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች በዓለም ላይ በስፋት እየተመረቱ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፥ “በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች በከተማ አካባቢ ስለሚንቀሳቀሱ እና ለእነሱም የቻርጅ ማድረጊያ መሰረተ ልማቶችን በቀላሉ ማዳረስ ስለሚቻል ተመራጭ ናቸው” ብለዋል።
ኢትዮጵያም ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ማንኛውም የግል መገልገያ የቤት መኪና በኤሌክትሪክ የሚሰራ እስካልሆነ ድረስ ወደ ሀገር ቤት መግባት እንደማይችል መወሰኗን አውስተዋል።
ይሁን እንጂ “ሰሞኑን አልሰማንም በሚል በነዳጅ የሚሰሩ አውቶሞቢሎች ገዝተው የሚመጡ አካላት አሉ” ያሉት ሚኒስትሩ፥ ተቋማቸው ከኤሌክትሪክ ውጪ በነዳጅ ለሚሰራ አዲስ የቤት አውቶሞቢል አገልግሎት እንደማይሰጥ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጥቅምት ወር 2014 ወደሀገሪቱ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይገቡ ከከለከለቻቸው 38 ምርቶች በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች መካተታቸው ይታወሳል።
ብሄራዊ ባንክ በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎችን ለማስገባት ለሚፈልጉ አስመጪዎች የባንክ መተማመኛ ሰነድ (LC) እንዳይከፈትላቸው ውሳኔ ማሳለፉም አይዘነጋም።
ለዚህም በዋናነት ተነስቶ የነበረው ምክንያት የአስመጪዎቹ የውጭ ምንዛሬ ዋነኛ ምንጭ የህገወጥ የምንዛሬ ገበያው እና ህገ ወጥ ሃዋላ በመሆኑ ክልከላው ህገወጥ የምንዛሬ ገበያውን ዝቅ ያደርገዋል የሚል ነበር።
ይሁን እንጂ ክልከላው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በስፋት እንዲገቡ ቢያደርግም በሁለት አመት ውስጥ ህገወጥ የምንዛሬ ገበያውም ዝቅ እንዲል ማድረግ አለመቻሉን ባለሙያዎች ያነሳሉ።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረጓን የገንዘብ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚህም የታክስ ማሻሻያ ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው መሆኑን ተነግሯል።
እንዲሁም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ ነፃ እንደሚደረጉም ሚኒስቴሩ ማስታወቁ አይዘነጋም።