በዓለም የወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ መጀመሪውን የወርቅና የብር ሜዳሊያዎች አገኘች
በወንዶች 3000 ሜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች 1ኛ እና 2ኛ ሆነው ተከታትለው በመግባት ወርቅና የብር ሜዳያ አስገኝተዋል
በሁለተኛ ቀን ውሎው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች ይጠበቃሉ
18ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች (ወጣቶች) አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬንያ አስተናጋጅነት በናይሮቢ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በትናትናው እለት በተጀመረው ውድድሩ ላይ የተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች ፍጻሜ ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት የወንዶች 3000 ሜትር አንዱ ነው።
በወንዶች 3000 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ላይም ኢትዮጵያን ወክለው የተወዳደሩት አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ውድድሩን በበላይነት ማጠናቀቅ ችለዋል።
በዚህም መሰረት አትሌት ታደሰ ወርቁ 7:42.09 በሆነ ሰዓት ውድድሩን 1ኛ ደረጃ በመያዝ በማጠናቀቅ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ሲያስገኝ፤ አትሌት አሊ አብዱልመና 7:44:55 በሆነ ሰዓት 2ኛ ደረጃን በመያዝ የብር ሜዳልያ አስገኝቷል።
ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በሁለተኛ ቀን ውሎው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የፍጻሜ ውድድሮች እንደሚጠበቁም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል።
በዚህም በ5000 ሜትር አዲሱ ይሁኔ እና መብራቱ ወርቅነህ የሚሳተፉበት የፍጻሜ ውድድር ከቀኑ 10፡30 እደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ መልክናት ውዱ የምትሳተፍበት የ3000 ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ውድድር ከቀኑ 11፡00 ላይ እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።
18ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች (ወጣቶች) አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ ከ400 ሜትር ጀምሮ በ8 የውድድር አይነቶች እንደምትሳተፍ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ፤ ከአጭር ርቀት ጀምሮ ወጣቶች በሚሳተፉባቸው የረጅም ርቀቶች፣ በ3000ሜ.መሰናክልና በእርምጃ ውድድሮች የምትካፈል ሲሆን በ10 ወንድ፣ በ15 ሴት እና በአጠቃይ በ25 አትሌቶች እንደምትወከል ከኢትጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።