ኢትዮጵያ ከቶኪዮ ኦሎምፒክ የመጀመሪዋን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች
አትሌት ሰለሞን ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 27 ደቂቃ ከ43 ሰከንድና ከ 22 ማይክሮ ሰከንድ ነው
ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሎምፒክ 2020 በ10ሜትር ውድድር የመጀመሪያዋን ወርቅ ያገኘችው በአትሌት ሰለሞን ባረጋ አማካኝነት ነው
በዛሬው እለት በተካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ 2020 ኢትዮጵያን በመወከል በ10ሺ ሜትር የፍጻሜ ውድድር የተሳተፈው አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣ ውድድሩን በ1ኛነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘት ችሏል፡፡ አትሌት ሰሎሞን ያገኘው ወርቅ የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ወርቅ መሆን ችሏል፡፡
አትሌት ሰለሞን ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ጊዜ 27 ደቂቃ ከ43 ሰከንድና ከ 22ማይክሮ ሰከንድ ነው፡፡በውድድሩ ከአትሌት ሰለሞን ባረጋ በተጨማሪ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻና አትሌት በሪሁ አረጋ ተሳትፈዋል፡፡
አትሌት ሰለሞን ከዚህ በፊት ያስመዘገባቸው ስኬቶች
አትሌት ሰለሞን ባረጋ፣በፈረንጆቹ በ2016 በዓለም ከ 20 ዓመት በታች በፖላንድ ባይድጎስዝ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳልያ ማሸነፉ የሚታወስ ሲሆን በ 2017 በአፍሪካ ከ 20 የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በአልጄርያ ትሌምቼን በ5ሺ ሜትርም የወርቅ ሜዳልያ ማስመዝገብ ችሏል፡፡
በተመሳሳይ በ 2017 በሁለት ውድድሮች ላይ አሸናፊ ሲሆን በ 2018 ም በአትሌቲክስ ሻምፒዮናና በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እንዲሁም በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ ነበር፡፡
ሰለሞን በ2018 በዳይመንንድ ሊግ በ5ሺ ሜትር አሸናፊ ሲሆን 12 ደቂቃ ከ 43 ሰከንድ ከሁለት ማይክሮ በሆነ ሰዓት ገብቶ ነበር፡፡ ሰለሞን በ2021 በኔዘርላንድስ ሄንግሎ በተወዳደረበት ወቅት 10 ሺ ሜትሩን በ26 ደቂቃ ከ 49 ሰከንድ ከ46 ማይክሮ ሰከንድ ገብቷል፡፡
ዛሬ በተካሄደው የ5ሺ ሜትር የማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያ የወከሉት አትሌት ጉዳፍ ጸጋየ፣ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪና አትሌት እጅጋየሁ ታየ ማጣሪያውን ማለፍ ችለዋል፡፡
በዘንድሮው የኦሎምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ፣በብስክሌት በውሃ ዋናና በቴኳንዶ የስፖርታዊ ውድድር አይነቶች ትሳተፋለች፡፡