ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቡድን ናይሮቢ ገባ
የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻሚዮን ከነሃሴ 11 እስከ 16 ቀን 2013 ዓ.ም በኬንያ ይካሄዳል
በሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ ከ400 ሜትር ጀምሮ በ8 የውድድር አይነቶች እንደምትሳተፍ ተገልጿል
በኬንያ ለሚካሄደው 18ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች (ወጣቶች) አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የሚሳተፈው የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ልዑክ ናይሮቢ ገብቷል።
ቡድኑ ናይሮቢ ጄሞ ኬኒያታ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር መለስ አለም አቀባበል እንዳደረጉላቸው ተገልጿል።
ውድድሩ ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ እስከ ዕሁድ ነሐሴ 16 ቀን 2013 ድረስ ይቆያል፤ ውድድሩ፤ ወጣት አትሌቶችን በዓለም አደባባይ ለማስተዋወቅና ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ልምድ እንዲቀስሙ ለማስቻል የሚደረግ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገለጻል።
በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ከ400 ሜትር ጀምሮ በ8 የውድድር አይነቶች እንደምትሳተፍ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፤ የፌዴሬሽኑ ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንትና የቡዱኑ መሪ፣ አትሌት ገዛኸኝ አበራ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በናይሮቢ የሚካሄደውን ውድድር በተመለከተ ትናንት መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም መሰረት ቡድኑ ለገጣፎ ለገዳዲ በሚገኘው አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ሆቴል ከአንድ ወር በላይ ስልጠናውን ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ፤ ከአጭር ርቀት ጀምሮ ወጣቶች በሚሳተፉባቸው የረጅም ርቀቶች፣ በ3000ሜ.መሰናክልና በእርምጃ ውድድሮች የምትካፈል ሲሆን በ10 ወንድ፣ በ15 ሴት እና በአጠቃይ በ25 አትሌቶች እንደምትወከል ከኢትጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዓለም ከ20 አመት በታች (ወጣቶች) አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዓለም አትሌቲክስ አዘጋጅነት እ.ኤ.አ ከ1986 ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ ለአምስት ወይም ስድስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ የመምና የሜዳ ተግባራትን ያካተተ ውድድር ነው።
በዚህ ውድድር ዕድሜያቸው ከ20 አመት በታች የሆኑ አትሌቶች ብቻ የሚወዳደሩም ይሆናል። ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ በተካሄዱት 17 የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በ37 ወርቅ፣ በ32 ብር፣ በ29 ነሃስ፣ በድምሩ በ98 ሜዳልያዎች ከዓለም አምስተኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
ከነዚህ ውስጥ 49 ሜዳልያዎች በሴቶች፣ 47ቱ ደግሞ በወንድ አትሌቶች የተመዘገቡ መሆናቸውን የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመለክታል።