ለቡድኑ ይፋዊ አቀባበል እንደሚዘጋጅ ተገልጿል
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘዉዴ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ከተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ቡድን ዝርዝር ሪፖርት እንደሚጠብቁ አስታወቁ፡፡
የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ልዑክ ቡድን ዛሬ ወደ ሀገር ቤት መግባቱን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫውም በቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተሳተፈው የኦሊምፒክ ልዑክ ቡድን ዝርዝር ሪፖርት እንደሚጠበቅ ገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ሣሕለ ወርቅ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ወደ ሀገር ቤት ለተመለሰው ቡድን የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” መልዕክት ማስተላለፋቸውን አል ዐይን አማርኛ ከፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ኢትዮጵያን በመወከል በየዉድድሩ ዘርፍ በተለይም በረጅም ርቀት ሩጫ ተሰልፈዉ የአቅማቸዉን በመፈጸም ወርቅን ጨምሮ ሌሎች ሜዳሊያዎችን ላስገኙ እና በአጠቃላይ በውድድሮች ላይ ለተሳተፉ አትሌቶች ምስጋናም ማቅረባቸውም ነው የተገለጸው፡፡
አትሌቶቹ ወደ ቶኪዮ ሲጓዙ እንደተደረገው የአሸኛኘት ሥነ ስርዓት ሁሉ ይፋዊ አቀባበል እንደሚኖርም ጽ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወከሎ የተሳተፈው ቡድን አዲስ አበባ ዛሬ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስም በመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
ቡድኑ በቶኪዮ ቆይታው አንድ ወርቅ፣ አንድ ብር እና ሁለት ነሐስ በድምሩ አራት ሜዳሊያ ይዞ ወደ ኢትተጵያ ተመልሷል፡፡