የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ
በ2016 ዓ.ም ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች 5.4 በመቶ ናቸው
1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ተማሪ አላሳለፉም ተሏል
የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ይፋ ሆኗል።
የ2016 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑ አስመልክቶ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫቸው፤ የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ 701 ሺህ 749 ተማሪዎች መካከል 684 ሺህ 205 ተማሪዎች መፈተናቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮ ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ ተማሪዎች መካከልም 36 ሺህ 409 ተማሪዎች ናቸው የማለፊያ ነጥብ ያመጡት ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ይህም አጠቃላይ ከተፈተኑት 5 ነጥብ 4 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን በተሰጠው ፈተና ከተፈተኑ ተማሪዎች 26.6 በመቶ የሚሆኑት ማለፋቸውን አስታውቀዋል።
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ሐረሪ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከአስፈተኗቸው ውስጥ የተሻለ ቁጥር ማሳለፋቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር ብርሃኑ አዲስ አበባ 10,690 ተማሪዎች በማሳለፍ ከፍተኛውን ስፍራ ይዟል።
በልላ በኩል ዘንድሮ 1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ እንዳላሳለፉ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል።
ተማሪዎች ውጤታቸውን መቼ እና እንዴት ማየት ይችላሉ?
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ የፈተናው ውጤት ለሊት 6 ሰዓት ላይ ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም መሰረት የ2016 ትምህርት ዘመን የኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቂያ (12ኛ ክፍል) ፈተና ውጤት እና የውጤት መግለጫ አድራሻ ይፋ ተደርጓል።
የ2016 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች ውጤታቸውን በሚከተሉት የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት የውጤት መግለጫ አማራጮች ከጳጉሜ 4 ቀን ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ ማወቅ ይችላሉ።
1. ፖርታል፡- https://result.eaes.et
2. በቴሌግራም ቦት (Telegram Bot):- https://t.me/EAESbot
3. በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS)፡- 6284 ላይ ‘R’ን በማስቀደም የመለያ ቁጥር በማስገባት (ምሳሌ R1234567) መልዕክት በመላክ ውጤትዎን ማወቅ ይችላሉ፤ ይህ አማራጭ ኢትዮ ቴሌኮም የሚያስከፍለው መደበኛ የSMS ክፍያ ይኖረዋል ተብሏል።
ከውጤት መግለጫ ፖርታልና ቴሌግራም ቦት ላይ ጊዜያዊ ሰርቲፊኬት ማውረድና ማታም የሚችሉ መሆኑም ተመላክቷል።
በተጨማሪም ተፈታኞች በውጤት እና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ቅሬታ ካላቸው ወደ አገልግሎቱ ቢሮ በአካል መምጣት ሳያስፈልግ ከSMS በስተቀር በውጤት መግለጫ አማራጮቹ ላይ Compliant የሚለውን በመጫን የቅሬታቸውን ዓይነት በተዘጋጀ የቅሬታ ፎርም ላይ በትክክል በመሙላት ማቅረብ ይችላሉ ተብሏል።