በአማራ ክልል የሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ከጥር አንድ ጀምሮ ተማሪዎቻቸውን እንደሚጠሩ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ
በአማራ ክልል ባለው ጦርነት ምክንያት ዩንቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ሳይጠሩ ቆይተዋል
አማራ ክልል ካሳለፍነው ሐምሌ ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ይገኛል
በአማራ ክልል የሚገኙ ዩንቨርሲቲዎች ከጥር አንድ ጀምሮ ተማሪዎቻቸውን እንደሚጠሩ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ትምህርት ይጀምራሉ ብሏል፡፡
ሚኒስቴሩ አክሎም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ክልል በተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች በ2016 የትምህርት ዘመን የመጀመሪያዉ ወሰነ-ትምህርት ተማሪዎቻቸውን ለመጥራትና መደበኛ የመማር ማስተማር ስራቸዉን ሙሉ ለሙሉ ለመጀመር አልቻሉም ነበር።
በመሆኑም የትምህርት ሚኒስቴር ከክልሉ ኮማንድፖስት፣ የጸጥታ አደረጃጀቶችና የሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ ፣ የአስሩ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንቶችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የክልሉ ጸጥታ አካላት ታህሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም በጉዳዩ ዙሪያ መክረዋልም ተብሏል፡፡
“በአማራ ክልል የድሮን ጥቃት” እንደሚቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ተናገሩ
ሚኒስቴሩ በመግለጫው አሁን ላይ በክልሉ አንጻራዊ ሰላም የተፈጠረ በመሆኑ ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎችን መጥራትና ማስተማር እንደሚችሉ ውሳኔ ላይ መደረሱን አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ከጥር 1 ቀን 2016 ጀምሮ ባሉ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ዩኒቨርስቲዎቹ ተማሪዎችን ጠርተው የመማር ማስተማር ስራቸውን ይጀምራሉ ተብሏል።
የፌደራል መንግስት “የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሶ ማደራጀት“ በሚል የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ማፍረሱን ተከትሎ ካሳለፍነው ሚያዚያ ጀምሮ ጦርነት ተከስቷል፡፡
ጦርነቱ መስፋፋቱን ተከትሎም የቀድሞው የክልሉ አስተዳድር የክልሉን ሁኔታ በመደበኛ የጸጥታ መዋቅር መቆጣጠር እንደማይቻል የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡