የትምህርት ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶች ማስክ በዞንና በወረዳ በኩል ሊያደርስ ነው
የፌዴሬሽን ም/ቤት የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ህግ አውጪ እና አስፈጻሚ አካላት ጋር ግንኙነት እንዳያደርጉ መወሰኑ ይታወሳል
ሚኒስቴሩ በትግራይ ክልል ላሉ ዞኖችና ወረዳዎች የተመደበላቸውን ማስክ እዲወስዱ ጥሪ ማስተላለፉን ገልጿል
የትምህርት ሚኒስቴር ለትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶች ማስክ በዞንና በወረዳ በኩል ሊያደርስ ነው
ትምህርት ሚኒስቴር ከከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ማስኮችን አዘጋጅቶ ለክልሎች ለማሰራጨት አዘጋጅቷል፡፡
በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን ማስኮችን በሚኒስቴሩ መዘጋጀታቸውን የትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሀረጓ ማሞ ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር የማስክ ክፍፍሉን ክልሎች ተረክበው ለትምህርት ቤቶች እንዲያደርሱ በፃፈው ደብዳቤ ላይ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ስም መዘለሉ እያነጋገረ ነው።
ወ/ሮ ሀረጓ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ ለትግራይ ክልል የተመደበውን ማስክ እንዲረከቡ ከክልሉ ዞኖች እና ወረዳዎች ጋር ጋር ግንኙነት አድርጓል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል ተቋማት በትግራይ ክልል ለሚያከናውኗቸው ተግባራት ግንኙነታቸውን በዞንና በወረዳ በኩል እንዲያደርጉ መወሰኑን ተከትሎ ነው ትምህርት ሚኒስቴር ክፍፍሉን በወረዳና በዞን ያደረግው። የዞኖቹ እና የወረዳዎቹ ምላሽ ምን እንደሆነ ላነሳንላቸው ጥያቄ ወ/ሮ ሀረጓ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሰሞኑ ባሳለፈው ውሳኔ የፌዴራል መንግስት እና ተቋማት ከትግራይ ክልል ህግ አውጪ እና አስፈጻሚ አካል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርጉ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግስት ለነዚህ አካላት የሚያደርገውን የበጀት ድጎማ እንዲያቆም እና ግንኙነቱ ከክልሉ የወረዳ ፣ የከተማ እና የቀበሌ አስተዳደሮች ጋር እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል፡፡