የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 40 በመቶ ብቻ ማለፋቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ
ሰኔ 30 የጀመረው የመውጫ ፈተና ለስድስት ቀናት ተሰጥቷል
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስፈተኗቸው ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 17 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው
ዘንድሮ የጀመረውን የከፍተኛ ትምህርት የመውጫ ፈተናን ከወሰዱ 150 ሺህ በላይ ተማሪዎች ውስጥ ያለፉት 40 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሰኔ 30 ጀምሮ ለስድስት ቀናት በተሰጠው የመውጫ ፈተና፤ 150 ሽህ 184 ተማሪዎች በኦንላይን ፈተናውን ወስደዋል።
ፈተናው በ215 መርሀ-ግብር መሰጠቱን ሚንስቴሩ ጠቅሷል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፤ 61 ሽህ 54 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን አልፈዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 48 ሽህ 632 ከመንግስት፤ 12 ሽህ 422 የሚሆኑት ተማሪዎች ደግሞ ከግል የትምህርት ተቋማት መሆናቸውን ተናግረዋል።
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስፈተኗቸው ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 17 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ተብሏል።
የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኸን እንደዘገቡት፤ 240 ሽህ ገደማ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሎ ቢገመትም፤ ለመፈተን ብቁ ሆነው የተመዘገቡት ግን 194 ሽህ ናቸው።
ከተመዘገቡት ተማሪዎች ውስጥ ለፈተና የተቀመጡት ደግሞ 150 ሺህ መሆናቸውን ሚንስቴር ዴኤታው ገልጸዋል።
ትምህርት ሚንስቴር የማለፊያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች ጥር ላይ ፈተናውን እንዲወስዱ ይደረጋል ብሏል፡፡