የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ሶስት ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነት ተነሱ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የተቋሙ ሶስት ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነት አንስተዋል
ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾመዋል
የኢሚግሬሽንና የዜግነት አገልግሎት ሶስት ከፍተኛ አመራሮች ከሀላፊነት መነሳታቸው ተገልጿል።
ፓስፖርት እና መሰል የዜግነት አገልግሎቶችን ለመስጠት የተቋቋመው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ተቋም ቅሬታዎች ሲቀርቡበት ቆይተዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ላለፉት አንድ ዓመት ከመንፈቅ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ የነበሩት አቶ ብሩህተስፋ ሙልጌታን፣ በምክትል ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ፍራኦል ጣፋ እና ታምሩ ግንበቶን ከኅላፊነት አንስተዋል።
የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ህዝብ ግንኙነት እና ኮሙንኬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ማስታዋል ገዳ ለአል ዐይን እንዳሉት ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ከሐምሌ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ መሾማቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሶናል ብለዋል።
እንዲሁም አቶ ጎሳ ደምሴ እና አቶ ቢቂላ መዝገቡ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንደተሾሙ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የተፈረመ ደብዳቤ ደርሶናልም ብለዋል።
- በኢትዮጵያ ፖስፖርት ማግኘት ቅንጦት ሆኗል ሲሉ ተገልጋዮች ተናገሩ
- በህገወጥ መንገድ ዜጎችን ወደ ውጭ ሲልኩ የነበሩ 16 የኢምግሬሽን አመራሮችና ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ
ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት አዲሱን ሹመት ከመቀበላቸው በፊት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዴኤታ ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ሀላፊ ሆነውም አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ በተለይም በያዝነው ዓመት አዲስ ፓስፖርት ለማግኘት አልያም ለማሳደስ የፈለጉ ዜጎች እየተጉላሉ መሆኑን አልዐይን ከሁለት ሳምንት በፊት ያነጋገራቸው አገልግሎት ፈላጊ ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል።
አገልግሎት ለማግኘት በሚልም በኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ያገኘናቸው ተገልግጋዮች እንዳሉን ከሆነ የፓስፖርት ጉዳይ የዜጎች መሰረታዊ መብት ቢሆንም ፓስፖርት ቅንጦት ሆኖብናል ብለዋል።
ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ ፖስፖርት ለማግኘት ጥረት ላይ መሆኗን የነገረችን ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አገልግሎት ፈላጊ በቀጠሮዋ ብትመጣም ድጋሚ ከሁለት ወር በኋላ እንደተቀጠረች አክላለች።
ድርጅቱ ባስቀመጠው የበይነ መረብ ማመልከቻ መሰረት አመልክቼ ሁሉንም የሚጠበቅብኝን ሁሉ አሟልቼ ባለፈው መጋቢት ፖስታ ቤት ሄጄ ፓስፖርቱን መውሰድ እንደምችል በተነገረኝ መሰረት ብሄድም ፖስታ ቤት የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ፓስፖርት ወደ እኛ መላክ ካቆመ ስድስት ወር እንዳለፈው ነግሮኛልም ብላለች።
"አሻራ እሰጠሁበት ክፍል መጥቼ ጉዳዩን ሳስረዳም ከሁለት ወር በኋላ ተመልሼ እንድመጣ በነገሩኝ መሰረት ድጋሜ ስመጣም አሁንም ለተጨማሪ ሁለት ወር አራዘሙብኝ" ስትልም በወቅቱ ነግራናለች።
ፓስፖርቱን በወቅቱ ባለማግኘቴ ብዙ እድሎችን አሳጥቶኛል ያለችን ይህች አስተያየት ሰጪ "የተወሰኑ ጓደኞቼ ገንዘብ ከፍለው በአጭር ጊዜ ውስጥ ወስደዋል እኔ የምከፍለው ገንዘብ ስለሌላለኝ እስካሁን ፓስፖርቱን አላገኘሁም" ብላለች።
ሌላኛዋ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አስተያየት ሰጪ በበኩሏ ልጇን ውጭ ሀገር ወደ ሚገኙ ዘመዶቿ በመላክ ማስተማር መፈለጓን ነገር ግን ፓስፖርቱ በመዘግየቱ ምክንያት ይህን ማድረግ እንዳልቻለች ገልጻለች።
ፓስፖርት ለልጄ እንዲሰጠን ያመለከትኩት ሰኔ ወር ላይ ወደ ውጭ ሀገር ሄዳ ነሀሴ ላይ እንድትጀምር ነበር ነገር ግን ድጋሚ መስከረም ወር ላይ እንዲመለሱ እንደተነገራቸውም አክላለች።
አገልግሎቱን ለማግኘት የሚጠየቀው ቅድመ መስፈርት በተለይም አሻራ ለመስጠት ለሚመጡ ሰዎች በቂ መረጃ አስቀድሞ አለመሰጠቱ ብዙ ሰዎችን እያንገላታ እንደሆነም ነግራናለች።
ፓስፖርት ማግኘት ለዜጎች ቀላሉ ነገር መሆን ነበረበት ያለን ደግሞ ሌላኛው አገልግሎት ፈልጊ ሲሆን ዜጎች ፓስፖርት ለማግኘት ከተቀመጡ ህጋዊ አሰራሮች ይልቅ አቋራጭ እና ህገወጥ መንገዶችን እንዲከተሉ ይበረታታሉም ብሎናል።
በድርጅቱ መግቢያ በር እና ዙሪያው ፓስፖርት በቀላሉ በአጭር ቀናት እናስጨርሳለን በሚሉ ደላላዎች የተሞላ መሆኑን የነገረን ይህ አስተያየት ሰጪ፣ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ደግሞ ፓስፖርት አስቸኳይ ጉዳዮች ላሏቸው ሰዎች ብቻ እንደሚሰጡ ተነግሮኛልም ብሏል።
የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት በበኩሉ አሁን ላይ ፓስፖርት እየሰጠ ያለው ለህክምና ወደ ውጪ ሀገር ለሚሄዱ፣ ስኮላርሽፕ እድል ላገኙ፣ ድቪ ሎተሪ ለደረሳቸው እና ለመንግስታዊ አገልግሎት ወደ ውጪ ሀገራት ለሚሄዱ ሰራተኞች እና አመራሮች ብቻ መሆኑን ገልጿል።
ፖስፖርት ለሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ ፓስፖርቱን ለምን መስጠት አልተቻለም? በሚል ላቀረብነው ጥያቄም ኢትዮጵያ የፓስፓርት ህትመትን በውጭ ሀገራት እንደምታካሂድ ነገር ግን ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ህትመቱን ያካሂድ የነበረው ድርጅት ላይ ጫና በመፈጠሩ የፓስፖርት እጥረት እንደተፈጠረም ገልጿል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት በረራ በመቀነሱ የፓስፖርት ህትመት ፍላጎት ቀንሶ ነበር ያለን ድርጅቱ ነገሮች ወደ ነበሩበት ሲመለሱ የፓስፖርት ህትመት ፈላጊ ሀገራት ቁጥር በመብዛቱ ኢትዮጵያ እንዲታተምላት ያዘዘችው ፓስፖርት በተፈለገው መጠን እና ጊዜ ውስጥ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ አይደለምም ብሏል።
እጃችን ላይ ያለውን የተወሰነ ፓስፖርት ለተመረጡ አስቸኳይ አገልግሎቶች እየሰጠን ነው የሚለው የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ክፍያ ፈጽመው፣ አሻራ ሰጥተው እና አስፈላጊውን መስፈርት ሁሉ አሟልተው ፓስፖርታቸውን ማግኘት ያልቻሉ ዜጎች እንዳሉ አስታውቋል።
ፍላጎቱን ማሟላት የሚያስችል ፓስፖርት ወደ ሀገር ውስጥ በቅርቡ እናስገባለን ያለው ድርጅቱ ከመስከረም 2016 ጀምሮም የፓስፖርት ጠያቂ ዜጎችን ፍላጎት እናሟላለን ሲልም ምላሽ ሰጥቶም ነበር።