ባለፉት 10 አመታት የጃፓን ፓስፖርት በከፍተኛ ተቀባይነት 1ኛ ሲባል ኢትዮጵያ 96ኛ ሆናለች
የዓለም የጉዞ ሰነድ ተቀባይነትን አስመልክቶ ቁጥራዊ መረጃና ደረጃን የሚያወጣው ሄንሌይ የተሰኘው ፓስፖርት መለኪያ ተቋም የመጀመሪያውን የአስር ዓመት ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
በዚህም መሰረት ጃፓን በ191 ሀገራት ከቪዛ ነፃ ጉዞ በመፍቀድ ወይም ተጓዦች ሲገቡ በቀጥታ ቪዛ (visa-on-arrival) በመስጠት ከዓለማችን ቀዳሚ ሆናለች።
ሲንጋፖር 2ኛ ፣ ደቡብ ኮሪያና ጀርመን ደግሞ እኩል ነጥብ በማምጣት 3ኛ ሆነዋል።
የአውሮፓዎቹ ጣሊያን እና ፊንላንድ 4ኛ ፣ ስፔን፣ ሉክሰምበርግ እና ዴንማርክ 5ኛ ፣ ስዊድን እና ፈረንሳይ 6ኛ እንዲሁም አየርላንድ 7ኛ ደረጃ በመያዝ በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።
አሜሪካና ብሪታኒያ ግን ከደረጃቸው ተንሸራተው ከአምስት ዓመት በፊት እ.ኤ.አ 2015 ላይ ከነበራቸው ቀዳሚ ደረጃ ወርደው 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትቶች በመለኪያው መሠረት ባለፈው አስር ዓመት ትልቅ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፣ 47 ደረጃዎችን በማሻሻል 18ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ መቻሏን የሄንሌይ እና አጋሮቹ የደቡብ ምሥራቅ ኢስያ ኃላፊ እና ተባባሪ ሥራ አስኪያጅ ዶሚኒክ ቮልክ ተናግረዋል።
ሪፖርቱ በነፃነት ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር መጓዝን አስመልክቶ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን፣ በተለይም እ.ኤ.አ ከ2006 ወዲህ ባሉት ዓመታት ልዩነቱ እየሰፋ መምጣቱን ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱ መሠረት አንድ የጃፓን ፓስፖርት የያዘ ሰው 165 ሀገራት በነፃነት መዘዋወር ሲችል፣ 107ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችውን የአፍጋኒስታን ፓስፖርት የያዘ ሰው ደግሞ 26 ሀገራት ብቻ ሲደርስ ቪዛ እንደሚመታለት ሪፖርቱ አትቷል።
የሄንሌይ ፓስፖርት መለኪያ ዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሚሰጠውን መረጃ ተመርኩዞ ደረጃ የሚያወጣ ሲሆን፣ የ199 ፓስፖርቶች እና 227 የጉዞ መዳረሻዎችን መረጃ ያካትታል።
በመለኪያው መሠረት ኢትዮጵያ 43 ሀገራት ከቪዛ ነፃ እንዲገቡ አሊያም የራሷ ዜጎች ወደ ሀገራቱ ሲገቡ ብቻ ቪዛ በማግኘት 96ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ምንጭ፡-ሲኤንኤን