በኢትዮጵያ የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ካርታ (ዲጂታል ማፕ) በይፋ ተመረቀ
በኢትዮጵያ የህዝብ ትራንስፖርት ለማሻሻል ወሳኝ ነው ተብሎ የሚታመነው የጉዞ እቅድ መተግበሪያ (ዲጂታል ማፒንግ) ዛሬ ታህሳስ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በሂሊተን ሆቴል የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።
የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር በተለይም የህዝቡ የትራንስፖርት ተጠቃሚነትና የማጓጓዝ አቅም በየዓመቱ በአማካይ በ9.3 በመቶ እድገት አሳይቷል፡፡ይሁን እንጂ የብዙሃን ትራንስፖርት አቅርቦቱ ካለው ፍላጎት አንጻር ውስንነት እንደነበር በመድረኩ ላይ ተገልጿል።
ለዚህም መፍትሔ ደግሞ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ መፍትሄ ይዞ መንቀቀሳቀስ እንደሚገባ ሚ/ር ዳግማዊት አስገንዝበዋል።
ወ/ሮ ዳግማዊት በከተማ መስፋፋት እና የህዝብ ቁጥር እያደገ መምጣት ጋር በተያያዘ አዳዲስ አካባቢዎች እና መኖሪያ ሰፈሮች መፈጠር፣ በዚህም የተነሳ አዳዲስ የጉዞ መስመሮች መፈጠር እንዲሁም የአውቶቡስ እና የታክሲ መስመሮችን ለማወቅ እና ለመጠቀም ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀው ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ከናይሮቢ (ዲጂታል ማታተስ) እንዲሁም የካይሮ ትራንስፖርት ተሞክሮን በመውሰድ ዛሬ የአዲስ አበባ የህዝብ ትራንስፖርት የጉዞ እቅድ መተግበሪያ ካርታ (ዲጂታል ማፕ) ላይ ማስፈር መቻሉን ገልጸዋል።
የጉዞ መተግበሪያውን ለማከናወን በዋናነት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲቲዩት እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ በመሆን የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር፣ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ የሸገር የብዙሀን ትራንስፖርት እና የከተማ የሚኒባስ ታክሲ የአገልግሎት መስመር መነሻ፣ የመተላለፊያ እና የመዳረሻ እንዲሁም ፌርማታ አካባቢ ቦታዎች መረጃን በአካል ተገኝቶ በመሰብሰብ ለማካተት ተችሏል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዛሬ በአዲስ አበባ ያስጀመረውን የጉዞ እቅድ መተግበሪያ (ዲጂታል ማፕ) በአጭር ጊዜ ውስጥ ከወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲቲዩት እና በየክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመሆን ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከተሞች እንደሚያስፋፋ ሚኒስትሯ መግለጻቸውን የትራንስፖርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።