በትግራይ ይካሄዳል የተባለው የኤጲስ ቆጰሳት ሹመት እንዲዘገይ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ
የፌደራል እና የትግራይ ክልል አመራሮች በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡም ተጠይቀዋል
የትግራይ አባቶች በነገው ዕለት የኤጲስ ቆጰሳት ሹመት እንደሚያከናውኑ መግለጻቸው ይታወሳል
በትግራይ ይካሄዳል የተባለውን የኤጲስ ቆጰሳት ሹመት እንዲያዘገይ የኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።
የኢትዮጵያ የሐይማኖት ጉባኤ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
ተቋሙ እንዳለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ የአለመረጋጋት ክስተት በተደጋጋሚ እያስተናገደች መሆኗ በእጅጉ አሳስቦኛል ብሏል፡፡
በተለይም ከሰሞኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትሪያርክን ጨምሮ አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የሰላም ልዑካን በትግራይ ክልል፣ በመቀለ ከተማ በመገኘት በክልሉ ካለው የቤተ ክርስቲኒቱ መዋቅር ጋር የተፈጠረውን የግንኙነት ችግር በመፍታት እርቀ ሰላምን ለማድረግ ታሳቢ ተተደረገው ጉዞ ዓላማ ሳያሳካ ወደ አዲስ አበባ መመለሱ እንዳሳዘነውም አስታውቋል።
በትግራይ ክልል የተፈጠረው ሁኔታ እጅግ ከባድና ፈታኝ እንደሆነ እንረዳለን፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባቶችም ከመነሻው ይህ ሁሉ ችግር ከመከሠቱ በፊት አለመግባባቱ በሰላምና በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈታ ጥሪ ስናደርግ ብንቆይም አስከፊውን ጦርነትና የእርስ በርስ እልቂት አስተናግደናል ብላል፡፡
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድርን በፌዴራል መንግስቱ መካከል በተካሄደው የሰላም ድርድር በተደረሠው ስምምነት መሠረት የጦርነት ምዕራፉን ተዝግቶ የሰላም ንግግሮችና ግንኙነቶች መጀመራቸውን በመልካም ጎኑ አንስቷል።
በፖለቲከኞች መካከል የተጀመረው እርቀ ሰላምም በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በመላው ማኅበረሰብ ተስፋፍቶ የሆነውን ሁሉ በይቅርታና እርቅ በማከም ሀገራዊና ሃይማኖታዊ አንድነታችን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ይመለሳል በሚል ሲጠብቅ መቆየቱንም ተቋሙ ገልጿል፡፡
ሕዝቡ በጦርነቱ የደረሠበትን በደልና ስቃይ ደጋግሞ በመንገር ሀገራዊ አንድነታችን እንዳይመለስና እንዳይፀና የሚፈልጉ አካላት ትግራይን ለመነጠል ተግተው እየሠሩ እንደሆነ ተረድቻለሁ ያለው ይህ ተቋም ድርጊቱን ኮንኗል፡፡
በተለይም በአቡነ ማትያስ መሪነት ወደ ትግራይ የተጓዘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ልዑካን ቡድንን መንፈሳዊ አቀባበል ባለማድረግ እና ለመወያየትም ፍቃደኛ ባለመሆን የተወሠደው አቋም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የበለጠ እንድንረዳ አስችሎኛል ብላል፡፡
በትግራይ ክልል የምትገኙ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አባቶችና ካህናት ባሳለፍነው አስከፊ ጦርነት የደረሠባችሁን ስቃይ፣ በደልና እንግልነት ታሪክ መዝግቦታል፤ ስቃይና በደላችሁም ይሠማናል፤ ይሁንና በሆነውና ስለሆነው ሁሉ በግልጽ በመነጋገርና በፍትህ አደባባይ ፍትህና ርትዕ መጠየቅ ተገቢ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ለመነጋገር ብሎም ለመደራደር ፍቃደኛ እንድትሆኑ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የመነጋገርና የመደራደር አማራጭን ዝግ በማድረግ የተወሠደው አቋም ከቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ አስተምህሮ ጋር የሚቃረን ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያንና በሀገር አንድነት የሚኖረው ውጤትም የከፋ እንደሚሆን ድርጅቱ አሳስባል።
የትግራይ ክልል ህዝብም የብዙ ታሪክ እና ገድል ባለውለታ መሆኑን አውቆ ልቡን ለይቅርታ፣ ክንዱንም ለእርቅ በመዘርጋት ታሪካዊ ስህተት እንዳይፈፀም መሪዎቹን ሊያሳስብ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋም ጉባኤ አሳስባል።
የፌዴራል መንግስት እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ከምንምና ከማንም በፊት ስኬታማ ድርድር በማድረግ ጦርነቱን ለማቋም የወሠዳችሁት ጥረት የበለጠ እንዲሳካ የሕዝብ ለሕዝብ እና የተቋማት ግንኙነት እንዲጠናከር ተገቢውን አመራር እንድትሠጡ ሲልም ጠይቋል።
እንዲሁም የትግራይ ክልል የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከማዕከላዊው መዋቅር ጋር የተፈጠረው አለመግባባት እና በክልሉ ለማከናውን የታቀደው ሹመትም በማዘግየት ይቅርታና እርቅ በማድረግ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንድታስጠብቁ ሲል ጥሪውን አቅርቧል።