የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ እርምጃ ምንድን ነው?
ቀኖናን በመጣስ የተወገዙ የቀድሞ አባቶች ከዐቢይ ጾም በፊል ውግዘታቸው በአዋጅ ይነሳል ተብሏል
"ያዘኑትን ማጽናናት" የተባለ ሐዋሪያ ጉዞ በኦሮሚያ ክልል እንደሚደረግ ተነግሯል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን "ባፈነገጡ" እና ኤጲስ ቆጶሳት ሾመናል ካሉ የቀድሞ አባቶች ጋር ተፈጥሮ የነበረው ችግር ቀኖናዊ ስርአቱን ተከትሎ መፈታቱን ስታውቃለች።
የካቲት ስምንት በቤተክርስቲያኒቱ ህግና ስርዓት መሰረት ተካሂዷል በተባለው ስምምነት በሀገር ሽማግሌዎች አቀራራቢነት ቤተክርስቲያን ወቅታዊ ችግሯን እልባት ለመስጠት ተስማምታለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ አቡነ ጴጥሮስ ለአል ዐይን አማርኛ ስለ ስምምነቱ ሲናገሩ "የቤተ ክርስቲያኒቷ አቋም ትክክል ነው፤ ተመለሱ ነው የተባለው፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ላይ የተመሰረተ ስምምነት ነው" ብለዋል።
በቤተ-ክርስቲያኗ የተወገዙት ሦስቱ ጳጳሳት ለፓትሪያርኩ ይቅርታ መጠየቃቸውንም ዋና ጸሀፊው አቡነ ጴጥሮስ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ውግዘቱ በፓትርያርኩ ሰብሳቢነት በሚደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ አማካኝነት የማንሳት ሂደቱ ይከናወናል ተብሏል።
የውግዘት አዋጁ የአቢይ ጾም ከመግባቱ በፊት (ከየካቲት 13 በፊት) በሚቀጥሉት ቀናት ይነሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ሳምንታትን በዘለቀው ወቅታዊ ችግር ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሀገረ ስብከት ሰራተኞች፣ አገልጋይ ካህናትና ምዕመናን ግድያ፣ እስራት፣ ወከባና እንግልት እንደተፈጸመባቸው ቤተ-ክርስቲያን ተናግራለች።
ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስና 12 ሊቃነ ጳጳሳት ከጠቅላይ ሚንስትሩና ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በነበራቸው ውይይት የታሰሩ አገልጋዮችና ምዕመናን እንደሚፈቱና መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንደሚታቀብ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ይሁን እንጂ ከዚህ ስምምነት በኋላ ታዋቂ የሚባሉ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች፣ ምዕመናንና ተሟጋቾች በጸጥታ ኃይሎች መታሰራቸው ታውቋል።
አብዛኞቹም ወደ አዋሽ ሰባት እስር ቤት እንደተጋዙና "በሽብር ተግባርና ህገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ተጠርጥረዋል" ተብሏል።
ቤተ-ክርስቲያን አንድነቴን ያስጠበቀ ባለችው የየካቲት ስምንቱ ስምምነት የታሰሩ ሰዎች ቀስ በቀስ እንደሚፈቱ ተነግሯል።
ስለ ስምምነቱ ገዥነት የጠየቅናቸው አቡነ ጴጥሮስ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሚቀጥሉት ቀናት ከቤተ-ክርስቲያን ጋር በተያያዘ የታሰሩት እንደሚፈቱ ቃል ገብተውልናል ብለዋል።
"በዚህ ጉዳይ የታሰሩ በሙሉ ወንጀል ቢኖርባቸውም እንኳ ከእናንተ ፊት አምጥተን ወንጀላቸውን አንብበን እኛ ኃላፊነት እንወስዳለን እስካላችሁ ድረስ እንለቃለን ብለው ቃል ገብተውልናል" ብለዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩን ቃል ገዥ እንደሆነ የተናገሩት አቡነ ጴጥሮስ፤ የሀገሪቱን መሪ ቃል እንደሚያምኑና ችግሩ እንደሚፈታም ገልጸዋል።
መንግስት በአንጻሩ ለቤተክርስቲያን ምን ያህል ይታመናል የሚለው ለመንግስት የሚጠየቅ ነው ብለዋል። "መንግስት ቃሉን ካላከበረ ከማዘን ውጭ የምለውም አይኖረኝም። ግን ደግሞ ያደርጉታል ብዬ አምናለሁ" ሲሉ ተስፋና እምነታቸውን ተናግረዋል።
እስከ ነገ አርብ (የካቲት 10) ድረስ የታሰሩ ሰዎች የመለቀቅ አፈጻጸም እንደሚታይ የገለጹት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊ፤ አንዳንድ አገልጋዮች እየተፈቱ መሆኑን አል ዐይን አረጋግጧል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አንድነቷንና ህልውናዋን ፈትኗል የተባለው "ህገ-ወጥ ሲመተ ጵጵስና" ውስጣዊ፣ ዘርና ፖለቲካን የተመለከተ መሆኑ አሳዝኖኛል ብላለች።
ይሁን እንጂ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ሌሎች ፈተናዎችን ተሻግሬ አልፊያለሁ፤ የአሁኑም ችግር ከችግርነቱ ባለፈ በጎ ውጤቶችን ይዞልኝ ብቅ ብሏል ብላለች።
የተፈጠረው ችግር በዋናነት የቤተ ክርስቲያንን ጥንካሬ ያሳየና ቀጣይ እርምጃዋን እንድትመለከት ማድረጉን አቡነ ጴጥሮስ ለአል ዔን አማርኛ ተናግረዋል።
"የምዕመኑ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን ቤተ ክርስቲያንን ያዩበት መንገድ፣ የምዕመኑ የእምነት መጠን፣ እምነት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል በዘመናችን ሰማዕታት ለመቀበል አንገታቸውን ለሰይፍ ደረታቸውን ለጥይት የሰጡ ክርስቲያኖች፣ ይሄ ቤተ-ክርስቲያን ህያው መሆኗን ያረጋገጥንበት ትልቅ እድል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሁለተኛ ቤተ ክርስቲያን በምናገለግለውና ቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገለገሉ ውስጥ ልዩነት አይተናል፤ ያሉት አቡነ ጴጥሮስ፤ ሦስተኛ ከዚህ ተነስተን ውስጣችንን እንድንመረምርና ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለብን፣ የተደበቀ የሰው ኃይል ወጥቷል፤ቤተ-ክርስቲያን ምን ያህል የሰለጠነ ኃይል አንዳላት ግልብጥ ብሎ ነው የወጣው፤ ቤተ-ክርስቲያንን ለማሳደግ እንደ እድል ቆጥረነዋል" በማለት የወቅታዊ ችግሩን ሌላኛ መልክ ገልጸዋል።
በቀጣይም በተፈጠረው ድርጊት ያዘኑ ምዕመናንን ማጽናናት፣ ጉዳት የደረሰባቸው አብያተ-ክርስቲያናት የመጠገ፣ የተበተኑትን የመሰብሰብ መርሀ-ግብር እንደሚካሄድ ዋና ጸሀፊው ገልጸዋል።
ተሾሙ የተባሉ ጳጳሳት ሲመለሱ በፓትርያርኩ መመሪያ ሰጭነት የቤተ-ክርስቲያኒቱ ቀኖና ስርዓት መሰረት አድርጎ በሂደት እየታየ መፍትሄ እንደሚሰጥ አቡነ ጴጥሮስ ተናግረዋል።
በየካቲት ስምንቱ ንግግር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ባለ 10 ነጥብ የመግባቢያ ሀሳቦች ላይ ተስማምታለች። በዋናነት ከቋንቋና ከአገልጋዮች ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስና የተጀመሩ ጥረቶችን ማጠናከር አጽንኦት ተሰጥቶታል።