ኢትዮጵያ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በራሷ ለማልማት የያዘቸው እቅድ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
በሀገር ውስጥ የለሙ ለመጠቀም የደረሱ የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) ፕላትፎርሞች አሉ
የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ለአል ዐይን አማርኛ ምላሽ ሰጥተዋል
የማህበራዊ ትስስር እና የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) መተግበሪያዎችን በራስ አቅም የማልማት ስራው በተጠናከ መልኩ መቀጠሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው አስታወቁ።
ፌስቡክና ትዊተርን ጨምሮ የተለያዩ የማህበራዊ ገጾች “ኢትዮጵያዊ እውነታ ይዘት ያላቸው፣ አንድነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን የሚሰብኩ ይዘቶችን ከገጻው የማጥፋትና እንዲህ አይነት ይዘት ያሏቸው መልእከቶችን የሚያሰራጩ ተጠቃሚዎች ገጾች እዘጉ ነው በመል የኢትዮጵያ መንግስት ሲከስ መቆየቱ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ ፌስቡክን እና ትዊተርን ሊተካ የሚችልና ቢያንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም የሚስያችል ሀገራዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የማልት እቅድ እንዳላት የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከዚህ ቀደም ለአል ዐይን መግለጻቸው ይታወሳል።
የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የማልማት ስራ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? በሚል ከአል ዐይን ለቀረበላቸው ጥያቄ የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው፤ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን እና መተግባሪያዎችን በራስ አቅም ማልማት ስራ ተጀምሯል ብለዋል።
“በራሳችን አቅም ያለማናቸውም፤ በተወሰኑ ተቋማት ደረጃ እየተጠቀምንባቸው ያሉ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያዎችም አሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
“ሆኖም ግን ወሰኖች አሉ፤ ፊትለፊት ላይ እና ከጀርባ የምናያቸው ነገሮች የተለያዩ ናቸው” ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ከጀርባ ከሚያስፈልጉት ውስጥ ትልልቅ የዳታ ማዕከላት፣ ኮኔክቲቪቲ እና የባንድ ዊድዝ ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
እነዚህ የዳታ ማዕከላት መረጃዎችን ለማጠራቀም፣ መልሶ ለመጠቀም አና ለተለያዩ አገልግሎቶች እንደሚጠቅሙም አስታውቀዋል።
አሁን ላይ የምንጠቀምባቸው ያሉ እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዩትዮብ እና መሰል የማህበራዊ ትስስር ገጾች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላይ ትልልቅ የዳታ ማዕከላት እንዳሏቸውም ለአብነት አንስተዋል።
አሁን ላይ ከዋትስአፕ ጋር ተመሳሳይነት ያለው፤ ደህንነቱ ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ የተግባቦት (የኮሙዩኒኬሽን) መተግበሪያ አልምተን እየተጠቀምን ነው ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ይህንን መተግበሪያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ቢጠቀሙት መረጃዎቻቸው ሄደው የሚያርፉበት ቦታ ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህንን የመረጃ ማከማቻ ለመገንባት ምናልባት ትንሽ ጊዜ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ግበዓት እና ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ለመጠቀም የደረሱ የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) ፕላትፎርሞች መኖራቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “እነዚህ የማህበራዊ ትስስር ገጾች አማራጭ ገጾች ሆነው ለማህበረሰቡ እና ለተቋሞቻችን እንዲያገለግሉ ይደረጋሉ” ሲሉም አስታውቀዋል።
ዶ/ር ሽመቴ አክለውም፤ በማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍ በራስ አቅም እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን እና ውጤት ማስገኘታቸውንም አስታውቀዋል።
ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከወራት በፊት በሰጡት መግለጫ፤ የማህበራዊ ትስስር እና የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) መተግበሪያዎችን ከማልማት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ያላት አቋም ሌሎችን በመዝጋት ሳይሆን አማራጭ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ማቅረብ አለብን የሚል ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች” ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ “ነጻ ሀገር ሆነን ቆይተናል፤ በቴክኖሎጂው ዘርፍም ነጻነታችንን ማሳየት አለብን በሚል እሳቤ ነው እየተሰራ ያለው” ማለታቸውም ይታወሳል።