ኢትዮጵያ የራሷ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ለማልማት የያዘቸው አቋም በቴክኖሎጂው ዘርፍም ነፃ ሀገር መሆኗን ለማሳየት ነው- ዶ/ር ሹመቴ ግዛው
የዲጂታል ሉአላዊነት ጉዳይ የአንድ ሀገር ብሄራዊ ሉአላዊነት ጉዳይ እስከመሆን መድረሱን ገልፀዋል
በኢትዮጵያ ውስጥ የለሙና ለመጠቀም የደረሱ የተግባቦት ፕላትፎርሞች ባለራቀ ጊዜ ውስጥ ለህዝቡ ይፋ ይሆናሉ ብለዋል
ኢትዮጵያ የራሷ የሆኑ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ለማልማት የያዘቸው አቋም በቴክኖሎጂው ዘርፍም ነፃ ሀገር መሆኗን ለማሳየት እንደሆነ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ተናገሩ።
ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ለአንድ ወር ሲከበር የነበረውን 2ኛውን የሳይበር ደህንነት ወርን መጠናቀቁን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም 2ኛውን የሳይበር ደህንነት ወር ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት ድረስ የሳይበር ምህዳሩ ላይ ንቃተ ህሊናን ለመፍጠር የሚያስችል ስራዎች መሰራታቸውንም አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ተቋማት በካሳይበር ጋር በተያያዘ ያሉባቸውን ከፍተቶች እንዲፈትሹ እና በየጊዜው ኦዲት እንዲያስደርጉ ከማደረግ አንጻር ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ መፍጠር ስራ መሰራቱንም አስታውቀዋል።
ዶ/ር ሹመቴ አክለውም የዲጂታል ሉአላዊነት ጉዳይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ አጀንዳ እሆነ መምጣቱን ያነሱ ሲሆን፤ “ዘግየት ብለን ወደ ዘርፉ እየገባን ያለን ሀገራት በጣም በጥንቃቄ መግባት አለብን” ብለዋል።
“የዲጂታል ሉአላዊነት ጉዳይ የአንድ ሀገር ብሄራዊ ሉአላዊነት ጉዳይ እስከመሆንም ደርሷል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “የራሳችንን እና ተቋሞቻችንን የሳይበር ደህንነት ማስጠበቅ ሲቻል የሀገርን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሆነም” አክለው አንስተዋል።
በሳይበር ምህዳሩ ላይ የሀገርን ሉአላዊነት ማስጠበቅ ደግሞ ለአንድ ቡድን አሊያም ተቋም የሚተው ሳይሆን፤ የሁሉም ኃላፊነት እና የየእለት ስራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የማህበራዊ ትስስር እና የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) መተግበሪያዎችን ከማልማት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ያላት አቋም ሌሎችን በመዝጋት ሳይሆን አማራጭ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ ማቅረብ አለብን የሚል ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ነች” ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ “ነጻ ሀገር ሆነን ቆይተናል፤ በቴክኖሎጂው ዘርፍም ነጻነታችንን ማሳየት አለብን በሚል እሳቤ ነው እየተሰራ ያለው” ሲሉም ተናግረዋል።
የተግባቦት መተግበሪያዎችን አሁን ላይ ለምተው እና ሙከራ ተደርጎባቸው የተወሰኑ ተቋማት ብቻ የሚጠቀሙባቸው አሉ ያሉ ሲሆን፤ በማህበራዊ ሚዲያ ዘርፍም በራስ አቅም እንዲሁም ከግሉ ዘርፍ ጋር በመቀናጀት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች መኖራቸውን እና ውጤት ማስገኘታቸውንም አስታውቀዋል።
ሆኖም ግን መተግበሪያውን ማልማት ብቻ በቂ አይደለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከመተግበሪያዎቹ ጀርባ ግዙፍ መሰረተ ልማቶች ያስፈልጋሉ፤ ለዚህም መንግስት ትኩረት ሰጥቶት እየሰራ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
አሁን ላይ ግን ለመጠቀም የደረሱ የተግባቦት (ኮሙዩኒኬሽን) ፕላትፎርሞች መኖራቸውን በማንሳት፤ ባለራቀ ጊዜ ውስጥ ለህዝቡ ይፋ ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል።
እንደ ፌስቡክ እና ትዊት ያሉ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እያራመዱ ያሉትን አቋም በተመለከተ ዶ/ር ሹመቴ፤ “በድረ ገጾቹ ባለቤቶች እና እዛ ውስጥ ባሉ ተዋናዮች እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ሆን ተብሎ ኢትዮጵያውያንን እና የኢትዮጵያን ወዳጆች እያጠቁ እንደሆነ ይታወቃል” ብለዋል።
አሁንም ቢሆን ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ መልክእቶች የሚተላፉባቸው ገጾችን መዝጋታቸውን ቀጥለውበታል፤ “እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ በቴክኖሎጂ አመጣሽ ሽብር አንሸነፍም” ሲሉም ተናግረዋል።
“በዚህ ጉዳይ ላይ ከፌስቡክ ጋርም ይሁን ከትዊተር ጋር ብዙ የምንነጋገርባቸውበርካታ ነገሮች አሉ፤ እንነጋገርበታለን” ሲሉመ ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂ ውጤቶች የነሱ ናቸው፤ ስለዚህ እኛ ሄድናበቸው እንጂ እኑ አልመጡብንም ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ስለዚህ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የራሳችን የሆነ ገጾችን እናዘጋጃለን” ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ሀሳቦች ያላቸው በግልም ይሁን በተለያዩ ተቋምት ውስጥ ያሉ አካላት ወደ ኢንሳ በመምጣት በጋራ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።