ኢትዮጵያ ፌስቡክንና ትዊተርን በሀገራዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የመተካት እቅድ እንዳላት አስታወቀች
በኢትዮጵያ ውስጥ የለሙ ዋትሳፕና ዙምን የሚተኩ የተግባቦት ፕላትፎርሞች ሙከራ የሙከራ ስራቸው ተጠናቀው ወደ ስራ ሊገቡ መሆኑን ዶ/ር ሹመቴ አስታውቀዋል
ፌስቡክና ትዊተር ኢትዮጵያዊ የሆነ እውነት የያዙና ተጽእኖ የሚፈጥሩ መልእክቶች ካሉ በአስቸኳይ እንዲጠፉ እያደረጉ ነው ብለዋል
ኢትዮጵያ ፌስቡክን እና ትዊተርን ሊተካ የሚችልና ቢያንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም የሚስያችል ሀገራዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የመተግበር እቅድ እንዳላት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) አስታወቁ።
ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ አንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለፖለቲካ ሀይሎች መጠቀሚያ ሆነዋል፤ አሁን ባለንበት ሁኔታም ፌስቡክ እና ትዊተርን ለአብነት ማንሳት ይቻላል ብለዋል።
“ኢትዮጵያዊ የሆኑ እና እውነትን የያዙ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚሰራጩ እና ተጽእኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ መልእክቶች ካሉ ፌስቡክ በአስቸኳይ እንዲጠፉ እያደረገ ነው” ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ ትዊተርም አሁን ጀምሯል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ እውነታ ይዘት ያላቸው፣ ለሀገር ግንባታ የሚውል፣ አንድነትን፣ ፍቅርን እና ሰላምን የሚሰብኩ ይዘቶችን የሚያሰራጩ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ገጾች እየተዘጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ፌስቡክ ከዚህ ቀደም ‘ከኢንሳ ጋር ይሰራሉ’ እና ‘የመንግስት ደጋፊ ናቸው’ በሚል የተለያዩ ገጾችን ዘግቻለሁ ማለቱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “ገጾቹ የምንም ይሁኑ የማን ትክክለኛ መረጃ እስከያዙ ድረስ መዘጋታቸው ተገቢ እና ፍትሃዊ አይደለም” ሲሉም አስታውቀዋል።
አሁን ላይ ተቋማቱ እየወሰዱት ያለው ተግባር ገጽ መዝጋት ነው ብሎ ለመውሰድ ይከብዳል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ “የገጾቹ አዘጋግ የዘመቻ መልክ ያለው ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ በተቃራኒ የሚሰሩ አካላት ደግሞ “ያለማንም ከልካይ ምንም ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው እንደፈለጉ መረጃ ስያሰራጩ” እንደሚስተዋልም አስታውቀዋል።
ዴሞክራሲን አስፍነናል፤ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ እኛ ነን በሚሉ ሀገራት የለሙ እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ሰዎች ሀሳባቸውን መግለጽ መብትን የሚከለክሉ ከሆነ ሌላ ችግር እንዳለ ማሳያ ነውም ብለዋል።
እነዚህን የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች የሆነ አካል ወይም መንግስት ሳይዛቸው አይቀርም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ችግሩን ለመቅረፍ ከሁለቱ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለመስራት ሙከራ እተደረገ ስለመሆኑም አስታውቀዋል።
እነዚህ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የኛ አይደሉም ያሉት ዶ/ር ሹመቴ፤ “የሚያዋጣን ነገር የራሳችን የሆነ ፌስቡክን እና ትዊተርን ሊተካ የሚችል እንዲሁም ቢያንስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም የሚስያችል የማህበራዊ ትስስር ገጽ መፍጠር ነው” በሚል እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የለሙ የተግባቦት (የኮሙዩኒኬሽን) ፕላትፎርሞች ወደ ሙከራ መግባታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አክለዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ለስብሰባ የሚሆኑ፣ የኮሙዩኒኬሽን እንዲሁም የመረጃ መለዋወጫ መተግበሪያዎች አሁን ላይ የለሙ እና በሙከራ ደረጃ እየተሰራባቸው ያሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አስፈላጊው መሰረት ልማት ተሟልቶላቸው በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚለቀቁ መሆኑንም ዶክተር ሹመቴ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።