በኢትዮጵያ ሦስተኛ ዙር የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስለ መከሰቱ ማሳያዎች ተገኝተዋል ተባለ
ከጥቂት ወራት በፊት ከ2 እስከ 3 በመቶ የነበረው በወረርሽኙ የመያዝ ምጣኔ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 12 በመቶ አድጓል
ዶ/ር ሊያ ታደሰ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል
3ኛ ዙር የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ስለመከሰቱ ማሳያዎች ተገኝተዋል ተባለ፡፡
በወረርሽኙ የመያዝ ምጣኔ አሻቅቧል ያለው ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙ ለ3ኛ ዙር ስለመከሰቱ የሚያሳዩ ምልክቶች መታየታቸውን አስታውቋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የወረርሽኙን ወቅታዊ ሁኔታ በማስመልከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው 3ኛው የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ስለመከሰቱ ማሳያዎች ታይተዋል ያሉ ሲሆን ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ዶ/ር ሊያ ባለፈው ሳምንት ብቻ 5 ሺ 547 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በጠቆሙበት መግለጫቸው 510 ሰዎች በጽኑ መታመማቸውንና 66 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የመያዝ ምጣኔ ከጥቂት ወራት በፊት ከሁለት እስከ ሦስት በመቶ የነበረው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ወደ 12 በመቶ ያደገ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፈው ቅዳሜ በቀን አንድ ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዙ የሚያመለክተው ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን ነው።
ቅዳሜ ዕለት የተመዘገበው ቁጥር ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከታዩት ከፍተኛው መሆኑ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ካልተደረገ ችግሩ ከዚህ የከፋ እንደሚሆን ሳይንሳዊ ትንበያዎች ማመልከታቸውንም ነው ዶ/ር ሊያ የተናገሩት።
የቫይረሱን ሥርጭት በተመለከተ በአገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በስብሰባዎች፣ በእምነት ተቋማትና በማህበራዊ መስተጋብሮች አካባቢ መዘናጋቶች ይስተዋላሉ።
“የችግሩ መውጫ ቁልፍ በእጃችን ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፤ ስብሰባዎችን በመቀነስ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፣ የእጅ ንጽህናችንን በመጠበቅ እና በመከተብ ራሳችንንና ቤተሰቦቻችንን ከቫይረሱ እንጠብቅ ብለዋል።
በአገሪቷ የቫይረሱን ስርጭትን ለመከላከል እየተሰጠ ያለው ክትባት የሚመለከተው ሁሉ መውሰድ እንዳለበት ማሳሰባቸውንም ነው ኢዜአ የዘገበው።
ቫይረሱ በብዛት ያልተከተቡ ሰዎችን እያጠቃ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ክትባቱ በአዲስ አበባ በሁሉም ጤና ጣቢያዎችና በክልሎች ጭምር እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል ጤና ሚኒስትሯ።
እስካሁን በኢትዮጵያ በዓለም የጤና ድርጅት ፈቃድ ያገኙ ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ክትባቱን አግኝተዋል፡፡
እስካሁን 212 ነጥብ 6 ሚሊዬን ሰዎች በቫይረሱ በተጠቁባት እና 4 ነጥብ 4 ሚሊዬን ሰዎች በሞቱባት ዓለም 4 ነጥብ 9 ሚሊዬን ክትባቶች ጥቅም ላይ መዋላቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡