ልዩልዩ
በዓባይ ውኃ እና በግድቡ ጉዳይ ኢትዮጵያን በመደገፍ የሚታወቁት ጥቁር አሜሪካዊው የመብት ተሟጋች በኮሮና ታመው ሆስፒታል ናቸው
ለሁለት ያህል ጊዜ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው እንደነበርም የህይወት ታሪካቸው ይጠቁማል
ጃክሰን ግብፅ በናይል ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን “ታሪካዊ መብት” የቅኝ ግዛት ዘመን መብት እንዲሁም የዐረብ ሊግን ጣልቃ ገብነት በመቃወምም ይታወቃሉ
በዓባይ ውኃ እና በኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያን በመደገፍ የሚታወቁት እውቁ ጥቁር አሜሪካዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጄሲ ጃክሰን እና ባለቤታቸው በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ሆስፒታል ናቸው፡፡
የ79 ዓመቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጃክሰን ባሳለፍነው ጥር ብዙዎች በተሳተፉበትና ብዙዎች እንዲከተቡ ባሳሰቡበት ይፋዊ ስነ ስርዓት የቫይረሱን ክትባት ወስደው ነበረ፡፡
ሆኖም አሁን በቫይረሱ ተይዘው ከ77 ዓመቷ ባለቤታቸው ዣኩሊዬን ጋር ህክምና ላይ ናቸው፡፡
ጃክሰን ምንም እንኳን የፓርኪንሰን ህመም ተጠቂ ቢሆኑም ጥቁሮች የኮሮና ክትባቶችን እንዲያገኙ ሲቀሰቅሱ እና ሲያስተምሩ ነበር፡፡
የድምጽ አሳጣጥ መብቶችን በተመለከተ የአሜሪካ ኮንግረስ የያዘውን አቋም እንዲተው ለማሳሰብ በያዝነው ወር መባቻ በካፒቶል ሂል ሲደረጉ ከነበሩ ሰልፎች ጋር ተያይዞ ለእስር ተዳርገውም ነበረ፡፡
ከወጣትነት ዕድሜአቸው አንስቶ ከዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጋር ስለ ሲቪል መብቶች በመሟገት የሚታወቁት ጃክሰን በዓባይን ውኃ እና በኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያን በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡
ግብፅ በናይል ውሃ ላይ አለኝ የምትለውን “ታሪካዊ መብት” የቅኝ ግዛት ዘመን መብት እንዲሁም የዐረብ ሊግን ጣልቃ ገብነት በመቃወምም ይታወቃሉ፡፡
የግድቡን ጉዳይ በተመለከተ በግብጽ እና በዐረብ ሊግ ተጽፈው ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የገቡ ደብዳቤዎችን ጉዳይ ጥቁር የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኮሚቴ (Congressional Black Caucus) እንዲቃወም ከአሁን ቀደም ጥሪ ማቅረባቸውም የሚታወስ ነው፡፡
ከፍ ያለ ተደማጭነት ያላቸው ቄስ (ሪቨረንድ) ጄሲ ጃክሰን ለሁለት ያህል ጊዜ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው እንደነበርም የህይወት ታሪካቸውን የተመለከቱ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡