በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው ተረጋገጠ
የጤና ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ ከ ቻይና የመጡ 4 የተጠረጠሩ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማእከል ተለይተዉ ክትትል እየተደረገላቸዉ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
ከተለዩት ተጠርጣሪዎች ሁለቱ የሳል እና የሙቀት ምልክት ያሳዩ ቢሆኑም በአሁኑ ሰአት ግን አልፎ አልፎ ሳል ከማሳየታቸዉ ዉጭ ሌላ የበሽታ ምልክት እንዳልነበረባቸውም ገልጾ ነበር፡፡
በወቅቱ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ምንም አይነት የህመም ምልክት ባያሳዩም ከቻይና ወረርሽኙ ካለበት ቦታ የመጡ መሆናቸዉ እና ምልክቱን ካሳየዉ ተጠርጣሪ ጋር ቅርብ ግንኙነትያላቸዉ በመሆኑ ተለይተዉ ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡
በዚህም መሰረት ከአራቱ ተጠርጣሪ ህመምተኞች የላብራቶሪ ናሙና ተወስዶ ለምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ ነበር፡፡ ከተወሰደው ናሙና በአገራችን በተደገላቸው ምርመራ ከ 5 አይነት የኮሮና ቫይረሶች ነጻ መሆናቸውን በወቅቱ ማወቅ ተችሏል።
ዛሬ ደግሞ የጤና ሚኒስቴር በኮሮና ቫይረስ በመያዝ የተጠረጠሩ አራት ኢትዮጵያውያን ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን ከደቡብ አፍሪካ በተላከው ውጤት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በተደረገው ምርመራ ውጤት አራቱም ኢትዮጵያውያን ከኖቭል ኮሮና ቫይረስ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጧል ብሏል ሚኒስቴሩ።