የኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ ካሉት 800 የእምነት ተቋማት መካከል 656 ከፕላን ዉጭ የተሰሩ ናቸው አለ
የክልሉ መንግስት በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆምና የእምነት ተቋማቱ በራሳቸው እንዲያፈሱ እንደሚደረግ አስታውቋል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አማኞችን የገደሉና ያቆሰሉ አካለት ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቋል
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከሰሞነኛ የሸገር ከተማ መስጂድ ፈረሳ ጋር በተያያዘ ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተደድር ጋር ምክክር አድርጓል።
በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱህፋ የተመራ ልዑክ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሸመልስ አብዲሳ ጽ/ቤት በመገኘት፤ በሸገር ከተማ እየተከናወነ ባለው የመስጊድ ፈረሳ ጉዳይ ላይ ዉይይት ማድረጉን አስታውቋል።
ለአምስት ሰዓታት ፈጅቷል በተባለው ውይይት፤ ምክር ቤቱ ውይይቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ “የሸገር ከተማ አስተዳደር ”ከፕላን ዉጭ ተሠርተዋል“ ያላቸውን መስጂዶች ለማፍረስ ሲነሳ የሚመለከተውን የእስልምና ጉዳዮች አካላትን አለማወያየቱ እና በተደጋጋሚ ጊዜ የቀረበለትን የውይይት ጥያቄ አለመቀበሉ ቅሬታ ቀርቦበታል።
የከተማ እቅዶች "ሰው ተኮር" መሆን እንዳለባቸው የጠቀሰው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ በሸገር ከተማ "ያለ ፕላን" በህገ-ወጥ ተሰርተዋል በሚል 22 መስጂዶች መፍረሳቸውን አሳውቋል።
ጉዳዩ አስቀድሞ መነጋገርና መፍታት እየተቻለ የሰው ህይወት መጥፋቱ እጅግ የሚያሳዝን መሆኑንም ምክር ቤቱ ጠቅሷል።
ምክር ቤቱ ሕዝበ ሙስሊሙ የሸገር ከተማ መስጂድ ፈረሳ ጋር በተያየዘ በተፈጠሩት ሁኔታዎች እጅጉን መጎዳቱንና ማዘኑን በማብራራት፤ ተገቢውን ካሳና የሞራል ሕክምና እንደሚያስፈልገውም ጠቁሟል።
ሰላማዊ ሙስሊሞች ላይ በመተኮስ የገደሉና ያቆሰሉ የጸጥታ አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑም ጠይቋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሸመልስ አብዲሳ፤ በጉዳዩ ላይ ቅድሚያ ውይይት አለመደረጉ ስህተት መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ በሸገር ከተማ ዉስጥ ካሉት 800 የሁሉም እምነት ተቋማት መካከል 656 የሚሆኑት ከፕላን ዉጭ የተሠሩ በመሆናቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ በኋላ በዉይይት የእምነት ተቋማቱ ራሳቸው መፍረስ ያለባቸውን እንዲያፈሱ እንጂ ከአሁን በኋላ መንግሥት በራሱ ማፍረስ እንደሚያቆም አስታውቀዋል።
ኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ ምንግስት ሸገር ከተማ የኃይማኖትን እሴትን መሰረት አድረጎ እንደሚገነባ መናገሩን መግለጫው ጠቅሷል።
የእሰልምናን ጨምሮ የሌሎችም ቤተእምነቶችም ተቋማት በብዛት በሸገር ከተማ ፕላን ዉስጥ እንደሚካተቱ የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህም አስፈላጊውን የቤተእምነት መሥሪያ መሬቶችን በፕላኑ መሠረት ለምዕመኑ እንደሚሰጥና በቆርቆሮ ሳይሆን የከተማዋን ፕላን የሚመጥን በርካታ ዘመናዊ መስጊዶች በከተማው እንዲሰሩ እንደሚፈልጉም ተናግረዋል። አክለውም በሸገር ከተማ ለኢስላማዊ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የሚሆን መሬት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።