ከጁምዓ ሶላት በኋላ በመርካቶ አካባቢ በተፈጠረ ረብሻ የ2 ሰዎች ሕይወት አለፈ
ህግ በማስከበር ስራ ላይ በተሰማሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ
በአዲስ አበባ አንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት በኋላ በሌሎች አካባቢዎች መስጂዶች መፍረስ ጋር በተያያዘ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል
በአዲስ አበባ ከተማ የአርብ (የጁምዓ) ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች መስጂዶች መፍረስ ጋር በተያያዘ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል።
ይህንን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ማምሻውን በሰጠው መግለጫ፤ “በመርካቶ አካባቢ በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሰው ሕይወት ሲያልፍ ህግ በማስከበር ስራ ላይ በተሰማሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል ብሏል።
ፖሊስ በመግለጫው፤ “ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ/ም ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አንዋር መስጂድ የጁምዓ ሶላት ከተጠናቀቀ በኋላ በሌሎች አካባቢዎች መስጂዶች ፈርሰዋል በሚል ምክንያት በመርካቶ ዙሪያ በተፈጠረ ረብሻና ግርግር የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ህግ በማስከበር መደበኛ ሥራ ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሷል” ብሏል።
በተለይም በተለምዶ ጋዝ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ተፈጥሮ በነበረ ግርግር ሁለት ግለሰቦች ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ሆስፒታል ከተላኩ በኋላ ሕይወታቸው ማለፉን ነው ፖሊስ በመግለጫው ያመለከተው።
እንዲሁም አራት ግለሰቦች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ህግን ለማስከበር በተሰማሩ 37 የፖሊስ አመራርና አባላት እንዲሁም 15 የሚሆኑ የተለያዩ የፖሊስ አጋዥ ሀይሎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና የተላኩ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ንብረትነታቸው የአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በሆኑ ሁለት አውቶቡሶች ላይ ጉዳት መድረሱንም ፖሊስ በመግለጫው አመላክቷል።
መነሻውን አንዋር መስጂድ ያደረገው ረብሻ በጋዝ ተራ ፣ ቆርቆሮ ተራ ፣ ሰባተኛ አካባቢ ፣ አመዴ እና በተለያዩ አካባቢ ለማዛመት የተሞከረ ቢሆንም በፀጥታ አካሉ ጥረት ረብሻው ሳይስፋፋ መቆጣጠር መቻሉንም ፖሊስ አስታውቋል።
በአንዳንድ ማህበራዊ ሚዲያዎች በአዲስ አበባ ከፍተኛ የሆነ ረብሻ እንደተነሳ ተደርጎ እየተናፈሰ ያለው መረጃ የተጋነነ ከመሆኑም ባሻገር አጋጥሞ የነበረው ብጥብጥ በቁጥጥር ስር ውሎ አካባቢው ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ መግባቱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
ጥብጡን በመምራትና በማስተባበር እንዲሁም ዋነኛ ተሳትፎ የነበራቸው 114 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ በህግ አግባብ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ፖሊስ በመግለጫው አመላክቷል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በበኩሉ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ “መብቱን በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ በወጣ ህዝብ ሙስሊም ላይ የተወሰደው እርምጃ ፍፅም ተቀባይነት የሌለው ሲል አውግዟል።
ምክር ቤቱ በመግለጫው “በኦሮሚያ ክልል በሸገር ሲቲ የመስጅድ ፈረሳ ባለመቆሙ ህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞውን በዛሬው እለት በአደባባይ ድምፁን በሰላማዊ መንገድ አሰምቷል” ብሏል።
“ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ተከትሎ በታላቁ አንዋር መስጅድ የፀጥታ አካል በወሰዱት ኢ-ህገ መንግስታዊ እና ኢ ሰብአዊ እርምጃ የሰው ሂይወት አልፋል፣ብዙሃን ቆስለዋል” ሲልም አስታውቋል።
በመሆኑም ይህንን አስከፊ ጥቃት የፈፀሙ እና ያስፈፀሙ የፅጥታ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ አጥብቀን እንጠይቃለን ።