መንግሰት "በተነሳው ረብሻ" የሦሰት ሰዎች ህይወት ማለፉን ገለጸ
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ጉባዔ ባወጣው መግለጫ የመንግስት የጸጥታ ኃይል በዛሬው እለት በአንዋር መስጅድ የወሰደውን እርምጃ "የኃይል እርምጃ" ነው ብሏል
ግብረ ኃይሉ ረብሻ ሲል በጠራው ችግር በንብረት ላይ እና ለፀጥታ ማስከበር በተሰማሩ 63 የጸጥታ አካላት ጉዳት መድረሱን ገልጿል
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግበረ ኃይል ባወጣው መግለጫ በዛሬው እለት በአንዋር መስጅድ በተፈጠረው ችግር የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉን እና የአካል ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
ግብረ ኃይሉ "ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ የሴራ ቡድኖች የሰላቱን ሰላማዊ ሥነ-ሥርዓት ለማስከበር በተሰማሩ የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት ለማድረስ በተነሳ ረብሻ የሦስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል" ብሏል።
ግብረ ኃይሉ ረብሻ ሲል በጠራው ችግር በንብረት ላይ እና ለፀጥታ ማስከበር በተሰማሩ 63 የጸጥታ አካላት ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
ግብረ ኃይሉ እንደገለጸው "ጸረ ሰላም ኃይሎች፣ የእምነቱ ተከታዮች በህጋዊ መንገድ ያነሱትን ጥያቄ ለእኩይ አላማቸው በመጥለፋ ረብሻውን" ለማስፉፉት ያደረጉትን ጥረት ተቆጣጥሯል።
አዲስ በተቋቋመው የሸገር ከተማ መስጅዶች እየፈረሱ ነው በሚል ነበር ባለፈው አርብ እለት ተቃውሞው የተደመረው።
በዛሬው እለትም ከሶላት በኋላ በተፈጠረ ችግር በምእመናን ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት ደርሷል።
የኢትዮጵያ ሀይማኖት ጉባዔ ባወጣው መግለጫ የመንግስት የጸጥታ ኃይል በዛሬው እለት በአንዋር መስጅድ የወሰደውን እርምጃ "የኃይል እርምጃ" ነው ብሏል።
ጉባዔ በጸጥታ ኃይሎች እርምጃ ማዘኑንም ገልጿል።
የአዲስ አበባ እስልም ጉዳዮች ከፍተኛ ምክርቤት የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ በፌስቡክ ገጹ "የምክርቤቱ ኘሬዝደንት እና አመራሮች የማረጋጋት ስራ በመስራት አንድ ሸሂድ (መስዋእት) የሆነ ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ ሆስቲታል" እንዲሄዱ መደረጉን ገልጿል።
በአንዋር መስጅድ ውጥ የነበሩ እና በችግሩ ምክንያት መውጫ አጥተው የነበሩ ወደ ቤታቸው ተሸኝተዋል ብሏል ምክርቤቱ።
ባለፈው አርብ የተከተውን ችግር ተከትሎ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዘጠኝ አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ችግሩን ለመፍታት ከመንግስት ጋር እንደሚነጋገር አሳውቆ ነበር።