የአዲሱ ሸገር ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች “ለዓመታት የኖርንበት ቤት እየፈረስብን ነው” አሉ
አዲሱ አስተዳደር ቤቶቹ ሲገነቡ እርምጃ ላልወሰደው የቀድሞው ልዩ ዞን አስተዳደር ኃላፊነት እንደማይወስድ ገልጿል
የሸገር ከተማ አስተዳደር “እስከ 80 በመቶው የከተማው ቤቶች በህገ-ወጥ መንገድ በመገንባታቸው ህግ ለማስከበር እያፈረስኩ ነው” ብሏል።
ጸሀይ [ለደህንነቷ ሲባል ስሟ የተቀየረ] ከሰባት ዓመታት የአረብ ሀገር ስራ በኋላ ማረፊያዋን ያደረገችው በቀድሞው የኦሮሚያ ልዩ ዞን በአሁኑ ሸገር ከተማ አስተዳደር ነበር።
ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ቤቷን ቀልሳ በ2010 ዓ.ም ኑሮዋን ኢትዮጵያ ስታደርግ ሰላምና እፎይታን በመሻት ነበር።
ሆኖም ጸሀይና እሷን መሰሎች በሽህዎች የሚቆጠሩ የአዲሱ ሸገር ከተማ ነዋሪዎች "ህገ-ወጥ" በሚል ያለ ማስጠንቀቂያ ለዓመታት የኖሩበት ቤታቸው በመንግስት እንደፈረሰባቸው ይናገራሉ።
ከአዲስ አበባ ወሰን የተቀነሱና በዙሪያው ያሉ ከተሞችን በ12 ክፍለ ከተሞችና 36 ወረዳዎች መዋቅር ተሰርቶ "ሸገር ከተማ" በይፋ ጥር አንድ 2015 ዓ.ም ተመስርቶ የመጀመሪያ ተግባሩ በሚመስል አኳኋን ጥር ሦስት ህገ-ወጥ ያላቸውን ቤቶች ማፍረስ ጀምሯል።
ጸሀይ ለገጣፎ የካ ሰዲ ክፍለ ከተማ ድሬ በሚባል ቀበሌ በ1998 ዓ.ም በተገዛችው መሬት የሰራችውን ቤት ጥር 12 2015 ዓ.ም በግሬደር እንደፈረሰባት ለአል ዐይን ተናግራለች።
"በአረብ ሀገር ሽማግሌ ጦሬ የነበረኝን አማጥጬ ነው ቤቱን የሰራሁት፤ ኮንዶሚኒየም ነበር የፈለኩት፤ ሰዎች እኛም እየኖርን ነው ብለው ወደ እዛ ሄድኩ” የምትለው ጸሃይ፤ ቤቴን ግሪደር ከስር መጥቶ ናደው” ትላለች።
በቅርቡ ቀዶ ጥገና እንዳደረገች የምትናገረው ጸሀይ፤ ከ200 ካሬና ቤቴ ብላ ያለፉት አምስት ዓመታትን ከኖረችበት ንብረቷ መለያየት የግድ ሆኖባታል፤ ቤት ተከራይታ መኖርም የግድ ብሏታል። "ሰው ሀገር ዜግነት ነበረኝ፤ በሀገሬ ግን ዘግነቴ ተወሰደ" ስትልም አቤቱታዋን አቅርባለች።
ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው የዚሁ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አንደ ጎረቤቶቹ ቤቱ ባይፈርስም፤ መቼ የሚለውን ግን በስጋት እየተጠባበቀ መሆኑን ለአል ዐይን ተናግሯል።
ባለ ትዳርና የልጆች አባት የሆነው ነዋሪ መሬት ከአርሶ አደር ገዝቶ ኑሮውን መመስረቱን ይናገራል።
የአካባቢው [ለገጣ ለገዳዲ፣ ሰንዳፋ] ስብጥር የአረብ ሀገር ተመላሾች፣ ግንበኞች፣ የቀን ሰራተኞች እንዲሁም የኑሮ ጫናን ለማምለጥ ከከተማ ያፈገፈጉ ሰዎች ናቸው በብዛት የሚኖሩት።
"ከመጋባታችን በፊት ባለቤቴ ሁለት ጊዜ አረብ ሀገር ተመላልሳ ነው ቤቱን የሰራነው” የሚለው ግለሰቡ፤ ከ15 ዓመት በላይ እና መኖራቸውን እና “አሁን ግን ቤታችን ሲፈርስ ለማየት ተራ እየጠበቅን ነው" በማለት ያስረዳል።
"ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ በሌሊት በላያቸው ላይ ቤታቸው ፈርሷል" ሲል የጎረቤቶቹን እጣ የሚናገረው ነዋሪው፤ የቤት እቃቸውን ይዘው ለመውጣት እንኳ'ኮቴ' እስከ 50 ሽህ ብር እንደሚጠየቁ ገልጿል።
ሸገር ከተማ ከይፋዊ ምስረታው በፊት በታህሳስ መባቻ ጀምሮ በቀድሞ መጠሪያው አለም ገና አካባቢ ህገ-ወጥ ያላቸውን ቤቶች ማፍረስ ጀምሯል። ጉዳዩን ለመመርመር ያቀኑ አራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰራተኞች ለስምንት ቀናት መታሰራቸው አይዘነጋም።
ከለገጣፎው እርምጃ ባለፈም በሱሉልታና በአዲስ አበባ አዋሳኝ አካባቢ ከሰሞኑን በነበረ የቤት ፈረሳ ግብግብ ፖሊስ ጥይት መተኮሱ ተነግሯል።
ቤታችን ፈረሰ ያሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ለእንባ ጠባቂ ተቋም ማስገባታቸውን ለአል ዐይን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም እርምጃውን "ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ" ብሎታል።
በዚህ የማይስማማው የሸገር ከተማ አስተዳደር "ዘመናዊ ከተማ ለመገንባት እየሰራሁ ነው” ብሏል። ህገ-ወጥ ግንባታ ከሰብዓዊነት ጋር መያያዙም ያሳዝነኛል ሲል አክሏል።
የከተማው ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ለአል ዐይን ሲናገሩ ከ70 እስከ 80 በመቶው የከተማው ቤቶች በህገ-ወጥ መንገድ የተገነቡ ቤቶች ናቸው ብለዋል።
ህግን ለማስከበርና ለከተማዋ እድገት ሲባል እርምጃው እየተወሰደ መሆኑን የሚገልጹት ከንቲባው፤ የቅርብ ጊዜ ቤቶችን ብቻ ነው እያፈረስን ያለነው ባይ ናቸው።
ነዋሪዎችና ኢሰመጉ ግን በዚህ አይስማሙም። ቤቶቹ ምንም እንኳ የክልሉ መንግስት ከ2005 ዓ.ም በፊት የተሰሩ የጨረቃ ቤቶች እንዳይፈርሱ ውሳኔ ቢያሳልፍም፤ አሁን እየፈረሱ ያሉት ግን ከ15 እስከ 20 ዓመት የነበሩ ቤቶች ናቸው ይላሉ።
ከንቲባ ተሾመ አዱኛ ግን ይህ ህግ እየተተገበረ መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል። ከንቲባው "መሬቱ መንግስት በሚፈቅደው አግባብ ካልወሰደና የግንባታ ፈቃድ ሳያገኝ ከተሰራ ህገ-ወጥ ነው" ብለዋል።
እርምጃውን ማስጠንቀቂያ ሰጥተንና ቤቶቹ ላይ ምልክት አድርገን ነው ማፍረስ የጀመርነው ሲሉም በነዋሪዎቹ ለተነሳው ወቀሳ ምላሽ ተሰጥተዋል።
ቤት ፈረሳው ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉንም ክውነት የራቀ ነው ያሉት ከንቲባው፤ የኮቴ ክፋያ ተጠይቋል መባሉንም "ውሸት" ብለዋል።
አዲስ አበባ ሳሪስ ዋና ቢሮዬን አድርጊያለሁ ላለው አስተዳደር አል ዐይን የቀድሞው አስተዳደር ህገ-ወጥ ግንባታ ሲደረግ የት ነበር? ለምንስ ወዲያውኑ እርምጃ አልወሰደም? ሲል ጠይቋል።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) "ስላለፈው ነገር መናገር አልፈልግም፤ ወደፊት መገንባት ስለምንፈልገው ነገር ነው ማውራት የምፈልገው፤ ስለባለፈው ውድቀታችን፤ ድክመታችን ሀሳብ መስጠት የለብኝም፤ አስፈላጊም አይመስለኝም። ትክክል ላይሆን ይችላል። ያ ትክክል ያልሆነው ነገር ደግሞ የማስተካከያ የሞራልና የህግ ግዴታ አለብን" በማለት ለቀድሞው አስተዳደር ችግር ኃላፊነት እንደማይወስዱ ተናግረዋል።
ግላዊና ማህበራዊ ህይወታቸውን ለዓመታት ሀገሬ ባሉት አካባቢ ገንብተው በህገ-ወጥነት ቤታቸው ለፈረሰባቸውና ህይወታቸው ለተናጋባቸው ሰዎች ምን መፍትሄ አስቀመጣችሁ ስንልም ለከንቲባው ጥያቄ አንስተናል።
ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) "ካሳችን ዘመናዊ ከተማ መገንባት ነው" በማለት መልሰዋል።
እስካሁን በሸገር ከተማ አስተዳደር የፈረሱ ቤቶች ቁጥር ይህ ነው ባይባልም፤ በአንድ ክፍለ ከተማ ብቻ ነዋሪዎች በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ቤቶች ሳይፈርሱ አልቀሩም ብለዋል።
ከንቲባው እርምጃችንን ሳንጨርስ መናገር አልፈልግም በማለት፤ ምን ያህል ቤቶች ፈርሰው ወደ መሬት ባንክ ምን ያህል መሬት ተመለሰ የሚለውን ከመናገር ተቆጥበዋል።