ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነውን የማዕድን ሀብቷን አታውቅም ተባለ
የማዕድን ሀብት ፍለጋን በቴክኖሎጂ ያካሂዳል ከተባለ የአሜሪካ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ
ስምምነቱ በዋናነት በሳተላይት የተደገፈ የስነ-ምድር መረጃዎችን ማቅረብ ላይ የተመሰረተ መሆኑ ተነግሯል
ኢትዮጵያ ትኩረት ነፍጋዋለች ከተባሉ ዘርፎች አንዱ ነው የተባለውን የማዕድን ዘርፍ ለማሳደግ በተለይም ከሁለት ዓመት ወዲህ እየሰራ መሆኑን መንግስት ተናግሯል።
ካለ ማዕድን እድገት የለም ያለው ማዕድን ሚንስቴር፤ የሀገሪቱን ሀብት ለማወቅ ጥረት እያደረገ መሆኑን አሳውቋል። ሀገሪቱ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የማዕድን ሀብቷን ማወቅ አለመቻለን የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገልጿል። ለዚህም የስነ-ምድር መረጃዎችን አለመገኘትና ፍለጋው ባህላዊ መንገዶችን ተከትሎ መካሄዱ ተነስቷል።
የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተር ጉታ ለገሰ የኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት ፍለጋና ጥናት ጉዞ ደካማ ነው ብለዋል። ፍለጋው በቴክኖሎጂ አለመደገፉና ሽፋኑ አነስተኛ መሆኑን ለማሳያነት ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ሀብት ብቻ መታወቁን ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ለፍለጋው አጋር ይሆናሉ ከተባሉ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራን ነው ብለዋል። የማዕድን ፍለጋ በአዲስ ቴክኖሎጂ ያሳልጣል ከተባለ የአሜሪካ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል።
“በጋራ የመስራት ፍላጎት” ነው የተባለው ስምምነቱ በጂኦሎጅካል ኢንስቲትዩት፣ በማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና ኦርየን አፕላይድ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተባለ ተቋም መካከል ነው።
ጉታ ለገሰ ስምምነቱ በራስ አቅም ይወስድ የነበረውን ረጅም የፍለጋ ጊዜ ያስቀራል ብለዋል።
ስምምነቱን የፈረመው ኦርየን አፕላይድ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የተባለው የአሜሪካ ተቋም በዋናነት በሳተላይት የተደገፈ የስነ-ምድር መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ተነግሯል።
“ሳተላይትን መሰረት ያደረገ የሀብት መጠቆሚያ ቴክኖሎጂ ነው የሚያቀርቡት። ስለዚህ በተለምዶ ከመፈለግ የሳተላይት ምስሎችን እየተጠቀሙ ሀብቱ የት እንዳለ በአጭር ጊዜ መጠቆም ከተቻለ የፍለጋ ጊዜያችንን ያሳጥርልናል። እና ተዘጋጅተን ሀብቱን ቶሎ የማግኘት ፍላጎት ስላለን ለዚህ ግብዓት ይሆነናል ብለን ነው የተፈራረምነው” ብለዋል።
የኦርየን አፕላይድ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የአፍሪካ የመርሀ-ግብር ኃላፊ ቴዎድሮስ ባህሩ በስምምነቱ ለኢትዮጵያ ብቻ የሚመደብ ሳተላይት እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል። የተገኙ የስነ-ምድር መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን እንደሚሰሩም ኃላፊው ገልጸዋል።
ለማዕድን ፍለጋው የተመደበው ሳተላይት ለግብርና፣ ለአየርን ንብረት ትንበያና ለኮሙኒኬሽን ግልጋሎትም ማዋል እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
ፍለጋው ትልቅ መዋዕለ-ነዋይ ጠያቂ መሆኑ ከወዲሁ የገንዘብ ችግር እንደ ትልቅ ፈተና ታይቷል።