በሱዳን የወርቅ ማዕድን ማውጫ ስፍራ ተደርምሶ 38 ሰዎች ሞቱ
ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን በባህላዊ የማዕድን ኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንደሚሰሩ ተገልጿል
በባህላዊ መንገድ የሚወጣው ማዕድን በሱዳን ከሚመረተው አጠቃላይ የወርቅ ምርት ውስጥ 75 በመቶውን የሚሸፍን ነው
በደቡባዊ ሱዳን ምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት የወርቅ ማውጫ ስፍራ ተደርምሶ ቢያንስ 38 ሰዎች መሞታቸውን የመንግስት ኩባንያ አስታወቀ።
የተደረመሰው የወርቅ ማዕድን ማውጫ የሚገኘው በምዕራብ ኮርዶፋን ግዛት የኤል ኑሁድ ከተማ ሲሆን፤ ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በስተ ምዕራብ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው።
የሱዳን ማዕድን ኃብት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ በኡሙ ድራይሳያ፤ በማዕድን ማውጫ መደርመስ ሳቢያ ህይወታቸውን ላጡ 38 ሰዎች ያላቸውን ክብርና አድናቆት ገልጿል፡፡
የምእራብ ኮርዶፋን ግዛት መንግስት እና የግዛቱ የጸጥታ ኮሚቴ፤ ስፍራው ለማዕድን ቁፋሮ አመቺ ባለመሆኑ ቀደም ሲል የማዕድን ቁፋሮውን ለመዝጋት ውሳኔ ላይ ደርሶ እንደነበር ኩባንያው መናገሩንም ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ውሳኔው ቢደረግም ግን የማዕድን አውጪዎች እንደገና ሰርገው ገብተው በማዕድን ማውጣት ስራ ውስጥ ሊሰማሩ ችሏል ነው የተባለው።
ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ሱዳናውያን ሰራተኞች በቀይ ባህር፣ ናህር አል-ኔል፣ ደቡብ ኮርዶፋን፣ ምዕራብ ኮርዶፋን እና ሰሜናዊ ክልሎችን ጨምሮ በባህላዊ ማዕድን ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሰማርተው ህይወታቸው እንደሚመሩ መረጃዎች ያሳያሉ።
በባህላዊ መንገድ የሚወጣው ማዕድን በሱዳን ከሚመረተው አጠቃላይ የወርቅ ምርት ውስጥ 75 በመቶውን እንደሚሸፍንና፤ ይህም በዓመት ከ93 ቶን እንደሚበልጥ አኃዛዊ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡