ከ4.7 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኙ የማዕድን ልማት ስምምነቶች ተፈርመው ወደ ስራ እንዲገቡ ተወሰነ
የሚኒስትሮች ምክር ቤት 100ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ አካሂዷል
ም/ቤቱ የፌዴራል የገቢ ግብር ደንብና የሠራተኞች ጡረታ ለመደንገግ በቀረቡት ረቂቅ አዋጆች ላይ ውሳኔ አሳልፏል
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 100ኛ መደበኛ ጉባዔው በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በቀረቡት ሰባት ከፍተኛ የማዕድን ልማት ስምምነቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ የኢንቨስትመንቶቹ መተግበር ከ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ እንደሚያስገኙ፣ ከ1 ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ አንዲሁም የአካባቢውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አስገዳጅ ድንጋጌዎች በስምምነቶቹ መካተታቸውን በማረጋገጥ ስምምነቶቹ እንዲፈረሙና ወደ ስራ እንዲገባ ወስኗል።
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወለድ አልባ የሆኑና የ1 ነጥብ 1 ቢሊዬን ዶላር ዋጋ ያላቸውን አራት የብድር ስምነቶች አጸደቀ
- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2013 በጀት ዓመት 26.4 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ
የተሀድሶ ህክምና አገልግሎት ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይም የተወያየ ሲሆን፤ አገልግሎቱ የተሀድሶ ህክምና መሳሪያዎችን በተለይም የሰው ሰራሽ አካላትን እና አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ማምረት እና አገልግሎቱንም በመላው ሀገሪቱ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በዘርፉ የልህቀት ማእከል በመሆን የሚያገለግል በመሆኑ በስራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።
ምክረ ቤቱ በተጨማሪም የፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች እና የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች ጡረታ ለመደንገግ በቀረቡት ረቂቅ ዐዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።