ዶ/ር አብይ “የግድቡ ጉዳይ መሰናክል ቢበዛበትም ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል በገባነው መሰረት እናከናውነዋለን” ብለዋል
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በሀገሪቱ የእንደራሴዎች ምክር ቤት በዛሬው እለት ምላሽ ከሰጡባቸው ጥያቄዎች የኢትዮ-ሱዳን ጉዳይ አንዱ ነው፡፡
ዶ/ር ዐቢይ ሁለቱም ሀገራት አሁን ላይ የራሳቸው ጣጣ ያለባቸው መሆኑን በመጠቆም “ጦርነት ፍፁም አያስፈልጋቸውም እናም ያላቸውን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ ይገባል” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሱዳን በታሪክ ላይለያዩ የተጋመዱ አንድ ህዝቦች መሆናቸውን ለምክር ቤቱ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሱዳን የኢትዮጵያ ጠላት መሆን አትችልም” ሲሉም ነው ለምክር ቤቱ የተናገሩት፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ መሰናክል ቢበዛበትም “ለኢትዮጵያ ህዝብ ቃል በገባነው መሰረት እናከናውነዋለን”ም ብለዋል ፡፡
ኢትዮጵያ አሁንም ያላትን ተፈጥሮአዊ ሀብት ከመጠቀም በዘለለ ግብፅና ሱዳንን የመጉዳት “አንዳችም ፍላጎት የላትም”ም ነው ዶ/ር ዐቢይ ያሉት፡፡
ለግብፅና ለሱዳን ወንድሞቻችን ይድረስ ሲሉም “እኛ ግድብን አልገደብንም፣ ከጣና የሚወጣው ውሀ አሁንም እየፈሰሰ ነው፣ እኛ እያልን ያለነው 86 በመቶ ድርሻ ቢኖረንም የክረምት ዝናብን እንጠቀም ነው፣ ይልቁንስ አብረን ብናድግ ይሻለናል” የሚል መልእክትም አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ ለመፈራረም ዝግጁ ናት” ብለዋል የግብጽና የሱዳን ዝግጁነት እንደሚያስፈል በመጠቆም፡፡
ሆኖም “ችግሩ ሙሌቱን ከውሃ አስተዳደር ጋር ማደባለቁ” ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
እንደ ዶ/ር ዐቢይ ማብራሪያ ከሆነ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት ስራውን በተያዘለት ጊዜ ካለስኬደች በየአመቱ 1 ቢሊዮን ዶላር ታጣለች፡፡
የግድቡ የድርድር ጉዳይ አሁንም ቢሆን መቋጫ ሳይበጅለት የዋለ ያደረ የሶስቱ ሃገራት የጋራ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል፡፡