“በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ኮንጎዎችን ለራሳችሁ ክብር ሊኖራችሁ ይገባል ብለናቸዋል”- አምባሳደር ዲና
ኢትዮጵያ ጉዳዩ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና በኮንጎው ፕሬዝዳንት እንዲጀመር ፍላጎት እንዳላትም ነው የገለጹት
አምባሳደሩ አያይዘውም “ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ስትገባ ምንም ያላለ ሀይል በውስጥ ጉዳይ ግቡ ውጡ ሲል ይገርማል” ሲሉ ተናግረዋል
የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአንድ ዓመት የሊቀ መንበርነት ሥራን በይፋ መጀመሯ ይታወሳል፡፡
ሊቀመንበርነቱን ከደቡብ አፍሪካ የተረከበችው ኮንጎ አፍሪካ ህብረትን በመወከል ካሉባት ተልዕኮዎች መካከል ዋነኛው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የሕዳሴ ግድብ ድርድር ነው፡
ይህንኑ ሥራ ለማከናወን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ሼስኬዲ ፕሬዝደንታዊ ፓናል ቡድን አቋቁመዋል፡፡
ይህ ፕሬዝዳንቱ ያቋቋሙት ቡድን በካይሮ እና በካርቱም ተገኝቶ ከተወያየ በኋላ አዲስ አበባ መምጣቱን የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የኮንጎ ልዑክ በቆይታው ምን አለ?
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ እንዳሉት ቡድኑ ከፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ፤ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ጋር ተወያይቷል፡፡
ፕሬዝዳንት ሼስኬዲ ያቋቋሙት ይህ ቡድን የካይሮና ካርቱም ቆይታውን አጠናቆ ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ በሀገራቱ የነበረውን ቆይታ በተመለከተ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት ገለጻ አድርጓል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት ግብፅ እና ሱዳንን በግድቡ ድርድር ላይ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ በድርድሩ እንዲሳተፉ ግብፅ እና ሱዳን መጠየቃቸውን ቡድኑ እንደገለጸ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያ፤ የአፍሪካ ሕብረት ሥራውን እየሰራ ባለበት እና ይህም ባላለቀበት ሁኔታ ሌላ አካል ማምጣት እንደማያስፈልግ መግለጿን አስታውቀዋል፡፡
አዲስ አበባ ሀሳቡን ከካይሮ እና ከካርቱም ይዞ የመጣውን የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ያቋቋሙትን ቡድን “እናንተም ለራሳችሁ ክብር ሊኖራችሁ ይገባል፤ እኛ ለአፍሪካ ክብር አለን፤ ክብር እንሰጣለን” ብለናቸዋል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ፤ ለአፍሪካ ካላት አክብሮት የተነሳ ጉዳዩ በወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር እና በኮንጎው ፕሬዝዳንት እንዲጀመር ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል፡፡ አዲስ አበባ ድርድሩ ቶሎ ይጀመራል የሚል ተስፋ እንዳላትም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሱዳንን ተቃዋሚ ትደግፋለች ወይ?
ኢትዮጵያ የሱዳንን አማጺያን እንደምትረዳ በሱዳን ዜና አገልግሎት እና በግብጹ አህራም ኦን ላይን ላይ የወጡት ዘገባዎችን በተመለከተ ኢትዮጵያ በየትኛውም ሉዓላዊ ሀገር ላይ ጣልቃ እንደማትገባ ገልጸዋል፡፡
በመተከልና ሌሎች አካባቢዎች የሲነሱ የነበሩ ግድያዎችን በተመለከተ የግብፅ እና ሱዳን ጣልቃ ገብነት እንዳለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጹን በተመለከተ በጉዳዩ ላይ ሌሎች የውጭ ሃይሎች የሉም ማለት አስቸጋሪ ነው ብለዋል ቃል አቀባዩ።
የግብፁ ፕሬዝዳንት የካርቱም ጉብኝት የሉዓላዊ ሀገር መብት መሆኑን ገልጸው ይህ ግን በኢትዮጵያ ኪሳራ እንዲሆን አዲስ አበባ “መቸም አትፈቅድም” ብለዋል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍ በትግራይ
በትግራይ ክልል እየተሰጠ ያለው ሰባዓዊ እርዳታ 70 በመቶ በመንግስት፤ 30 በመቶ ደግሞ በእርዳታ ሰጭዎች እንዲሸፈን የሆነበት ምክንያት በመንግስት ፍላጎት እንዳልሆነም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡
ይህንን የወሰነው “ረጂ ነኝ ሲል የነበረው ሃይል ነው እንደዛ ያደረገው፣ ግን አንዳንዱ ዕርዳታ ሳያመጣ ነበር ዝም ብሎ ሲጮህ የነበረው“ ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሱዳን፤ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መግባቷን በግልጽ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባሳወቀችበት ወቅት “ጉዳዩን ከቁብ ያልቆጠረ ሃይል ህግ አስከብራችኋል ብሎ ውጡ፣ ክፈቱ ሊል አይችልም“ ብለዋል፡፡
ድርጅቱ ይህንን የሚያደረገው ጫና ለመፍጠርና ታዳጊ ሀገራት የፖሊሲ ነጻነት እንዳይኖራቸው ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ባለፈው ሳምንት በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ አንገባም ላሉት “ምስጋና እናቀርባለን“ ሲሉም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።