በስምምነቱ "የተጣሰ ሕግና የተሰበረ እምነትም የለም"- የኢትዮጵያ መንግስት
ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነት እና አለምአቀፍ ህጎችን ጥሳለች የሚል ተቃውሞ አሰምታለች
መንግስት እንደገለጸው ይህ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት "ታሪካዊ ጥያቄዎች" የሚመልስ እና ስትራቴጅካዊ አጋርነትን ለመገንባት የሚያስችል ነው
በኢትዮጵያ መንግስት እና በራስ ገዟ ሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የጣስው ሕግ እንደሌለ ኢትዮጵያ አስታወቀች።
መንግስት ይህን ያለው በትናንትናው እለት የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሼህ መሀሙድ፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነት እና አለምአቀፍ ህጎችን ጥሳለች የሚል ተቃውሞ ማስማታቸውን ተከትሎ ነው።
- ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነትና አለማቀፉን ህግ ጥሳለች - ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ
- ኢትዮጵያ ወደብ እንድትከራይ እና በምላሹ ለሶማሊላንድ እውቅና እንድትሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ሶማሊላንድ አስታወቀች
የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ "በዚህ ስምምነት የሚጎዳ አካልም ሆነ ሀገር የለም። የተጣሰ ሕግም ሆነ የተሰበረ እምነት የለም" ብሏል።
መንግስት "ቢዚህ አዎንታዊ ድምዳሜ(ስምምነት) የሚከፋ፣የሚደነግጥ እና ሁኔታውን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀስ አካል" ሊኖር እንደሚችል ገልጿል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሶማሊላንድ የበርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ እንዲኖራት የሚፈቅድ የመግባቢያ ሰነድ ስትፈራረም ኮሽታ አልነበረም ያለው መንግስት "ወታራዊ ቤዝ እና የማሪታይም አገልግሎት በሰጥቶ መቀበል እና በከራይ" ለማግኘት የተፈራረመችውም ተመሳሳይ ነው ብሏል።
መንግስት እንደገለጸው ታሪካዊ የተባለው ይህ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት "ታሪካዊ ጥያቄዎች" የሚመልስ እና ስትራቴጅካዊ አጋርነትን ለመገንባት የሚያስችል ነው።
መንግስት ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው በጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ለወራት ምክክር ካደረገ በኋላ መሆኑን ገልጿል።
መንግስት እንደገለጸው ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ የባህር ኃይል እና ኮመርሻል አገልግሎት በሊዝ እንድትከራይ እድል የሚያስገኝ ሲሆን ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየርመንገድ ድርሻ እንዲኖራት ያስችላል።
ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና መስጠት ጉዳይን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት አጢኖ አቋም ለመውሰድ መስማማቱን ገልጿል።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሁለት ቀናት በፊት በፌስቡኬ ገጹ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እውቅና እንድትሰጣት እና በምትኩ 20 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የባህር ጠረፍ ለ50 አመታት እንድከራይ ስምምነት ላይ መደረሱን ግልጽ አድርጓል።
በዚህ ስምምነት ክፉኛ የተቆጣችው ሶማሊላንድን የራሷ አካል አድርጋ የምታያት ሶማሊያ፣ የኢትዮጵያ የሚገኙ አምባሳደሯን በትናንትናው እለት ወደ ሞቃዲሹ እንዲመለሱ ጠርታለች።
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሀሰን ሸህ መሀመድ በስምምነቱ ጉዳይ ለመምከር በተጠራው ፖርላማ ፊት ባደረጉት ንግግር ስምምነቱ "ህገወጥ እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው"ሲሉ ተናግረዋል።
ስምምነቱ የሶማሊያን ሉአላዊነት ጥሷል የሚሉት ፕሬዝደንቱ አጋርነት ለማግኘት የግብጽ እና የኳታር መሪዎችን በስልክ አነጋግረዋል ተብሏል።
ንግግሩን ተከትሎ የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ በቃል አቀባያቸው በኩል በሰጡት መግለጫ ግብጽ ሶማሊያ ሉአላዊነቷን እንድታስከብር ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል፡፡