ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነትና አለማቀፉን ህግ ጥሳለች - ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ
ፕሬዝዳንቱ ለሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ሶማሊያውያን የውጭ ጣልቃገብነትን ለማስቆም በጋራ እንዲነሱ ጥሪ አቅርበዋል
ሶማሊያ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን የመግባቢያ ስምምነት አጥብቀው ተቃውመዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፥ ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነት እና አለማቀፍ ህጎችን መተላለፏን ገልጸዋል።
ሶማሊላንድ በ1991 ነጻነቷን ብታውጅም ሞቃዲሾ አሁንም ድረስ የግዛቴ አካል ናት ብላ ታምናለች።
በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት አዲስ አበባ ለሃርጌሳ እውቅና እንድትሰጥ ያደርጋል መባሉ የሶማሊያ መንግስት አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ እንዲያደርግ አስገድዷል።
የሶማሊያ መንግስት በአዲስ አበባ የሚገኙትን የሀገሪቱን አምባሳደር አብዱላሂ ሞሀመድ ዋርፋ ወደ ሞቃዲሾ በዛሬው እለት እንዲመለሱ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ለሀገሪቱ ፓርላማው ያደረጉት ንግግርም ሶማሊያ ለጉዳዩ የሰጠችውን ትኩረት አሳይቷል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነት መዳፈሯንና ሶማሊያውያን “ለውጭ ጣልቃገብነትና የሀገርን አንድነት ለሚፈታተን ጉዳይ” በጋራ እንዲነሱ ጥሪ ማቅረባቸውን የሀገሪቱ የዜና ወኪል ሶና አስነብቧል።
ኢትዮጵያ በሶማሌ ውሃ ላይ ወደብ ለማቋቋም የሚያስችላት ስምምነት “ህገወጥ እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል” ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ለዘመናት ድንበር ተጋርተው የኖሩት ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ ጦርነት ውስጥ መግባታቸውን በማውሳትም ከሶማሊላንድ ጋር የተደረሰው ስምምነት የሀገራቱን ግንኙነት እጅጉን ሊያውከው እንደሚችል አብራርተዋል።
“እኛ ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላማዊና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን እንመርጣለን፤ ኢትዮጵያውያንን የሚከፋፍልን ነገርም አንፈልግም፤ ከኢትዮጵያ በኩል የተመለከትነው ግን ከምንጠብቀው በተቃራኒው ሆኗል” ማለታቸውንም ነው ሶና የዘገበው።
የኢትዮጵያ ተግባር በማህበረሰቡ ውስጥ አክራሪ አመለካከትን በማስፋት ውጥረቱን ሊያባብሰው ይችላል የሚል ስጋታቸውንም አጋርተዋል።
የሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዛ አብዲ ባር በሰጡት መግለጫም ሶማሊያውያን እንዲረጋጉና የሀገራቸው መንግስት የሶማሊያን የየብስ፣ ባህር እና አየር ድንበር እንደማያስደፍር መናገራቸው ይታወሳል።
ሞቃዲሾ ከኢትዮጵያ ጋር የከረረ ግጭት ውስጥ ከመግባታችን በፊት የጸጥታው ምክርቤት እና የአፍሪካ ህብረት በጉዳዩ ዙሪያ እንዲመክሩበት አሳስባለች።