ኢትዮጵያ ወደብ እንድትከራይ እና በምላሹ ለሶማሊላንድ እውቅና እንድትሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ሶማሊላንድ አስታወቀች
ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል
ስምምነቱ ኢትዮጵያ 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ለ50 አመታት በሊዝ እንድትከራይ እንደሚያስችላት መግለጫው ጠቅሷል
ኢትዮጵያ ወደብ እንድትከራይ እና በምላሹ ለሶማሊላንድ እውቅና እንድትሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ሶማሊላንድ አስታወቀች።
ከሶማሊያ የተገነጠለችው የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ለባህር ኃይሏ የሚሆን ወደብ እንድትከራይ እና ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ ይፋዊ እውቅና እንድሰጥ ሰምምነት ላይ ተደርሷል።
ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ስምምነቱ ለሶማሊላንድ ጠቃሚ የዲፕሎማሲ ምዕረፍ ነው ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለባህር ኃይላቸው ወደብ ሲፈልጉ ነበር ያለው ሚኒስቴሩ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ደግሞ የኢትጵያን እውቅና ለረጅም ጊዜ ጠብቀዋል ብሏል።
ይኸው የሚኒስቴሩ መግለጫ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ "ዛሬ በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስምምነት መፈረሙን ሳሳውቅ በታላቅ ደስታ ነው። ኢትዮጵያ 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ለ50 አመታት በሊዝ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ ይፋዊ እውቅና እንድትሰጥ ተስማምተናል" ማለታቸውን ጠቅሷል።
ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ አለምአቀፍ እውቅና በመስጠት የመጀመሪያ ሀገር ትሆናለች ብሏል።
ሶማሊያ እንደራሷ ግዛት አድርጋ የምታያት ሶማሊላንድ ራሷን ብታስተዳድርም አለምአቀፍ የሀገርነት እውቅማ ማግኘት አልቻለችም።
የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጽ/ቤት ያወጣው መግለጫ ዝርዝር ጉዳዮችን አልገለጸም።
ጽ/ቤቱ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎቷን ለማሳካት መንገድ የሚጠርግ እና የወደብ አማራጮችን የሚያሰፋ የመግባቢያ ሰነድ ከራስ ገዟ ሶማሊያላንድ ጋር መፈራረሙን ነበር የገለጸው።
የጠ/ሚኒስትሩ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በሊዝ ወታደራዊ ካምፕ እንድታገኝ መንገድ የሚከፍት መሆኑን እና በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምትወስድ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
ነገርግን አቶ ሬድዋንም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ስለመስጠት ጉዳይ አልተናገሩም።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ስለአየር መንገድ ድርሻ መውሰድ ጉዳይ አልጠቀሰም።
የሶማሊያ ካቢኔ በዛሬ ስብሰባው በወደብ ስምምነት ላይ ምላሽ እንደሚሰጥ የሶማሊያ የዜና አገልግሎት (ሶና) ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የባህር በር ለመጠቀም እንደምትደራደር መናገራቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት ኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ እንዲፈቅዱ፣ ከላሆነ ግን ቆይቶ ሊፈነዳ የሚችል የጸጥታ ችግር እንደሚሆን አሳስበውም ነበር።
ይሁን እንጅ ሶማሊያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ጥሪ አልተቀበለችም።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውቅቱ ባወጣው መግለጫ "የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት- መሬት፣ ባህር እና አየር- ቅዱስ እና ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው" ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።