ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ትኩሳት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል
ግብጽ ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም አስታወቀች፡፡
ኢትዮጵያ ከትናንት በስቲያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ያደረገችው ስምምነት በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ትኩሳት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነ ሲሆን ሀገራት በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ሱማሊላንድ አንድ አካሌ ናት የምትለው ሶማሊያ ስምምነቱን እንደ ወረራ እንደምትመለከተው ገልጻ ተመድ፣ አፍሪካ ህብረት ፣ የአረብ ሊግ እና ሀገራት ከጎኗ እንዲቆሙ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ ከግብጽ እና ኳታር አቻቸው ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ ጋ በስልክ መወያየታቸውን የገለጹ ሲሆን ግብጽም ከሶማሊያ ጎን እንደምትቆም ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት አልሲሲ በቃል አቀባያቸው በኩል በሰጡት መግለጫ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንደምታከብር እና ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ሞሃመድ ኦመር ወደ ኬንያ በማቅናት ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋር እንደተነጋገሩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነትና አለማቀፉን ህግ ጥሳለች - ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ በጉዳዩ ዙሪያ በወጣው መግለጫ ህብረቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንደሚያከብር ገልጿል፡፡
የሶማሊያ ሉዓላዊነት መከበር አለበት ያለው የአውሮፓ ህብረት የሀገር አንድነትን ለማክበር የሶማሊያን ህገ መንግስት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ተመድ ህግጋቶችን ማክበር ያስፈልጋልም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ኢትዮጵያ እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚዘልቅ ወደብ እና ወታደራዊ ማዘዣ መገንባት የሚስችላት ሲሆን ለሶማሊላንድ ደግሞ የሀገርነት እውቅና እንዲሰጥ ይደነግጋል ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ልገለል አይገባም፣ ከ100 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠትም የበህር በር ያስፈልገኛል ማለቷ ይታወሳል፡፡