የኢትዮጵያ መንግስት 2ኛ ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት መጀመሩን ለግብጽ ማስታወቁን ግብጽ ይፋ አድርጋለች
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን 2ኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጀመሯን አሳውቃኛለች ሲል የግብፅ ውሃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስትሩ መሐመድ አብደል አቲ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መጀመሯን ለግብጽ ማሳወቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግድቡ ውኃ ሙሌት መጀመሩን የሚገልፅ ደብዳቤ ከአዲስ አበባ እንደተላከላቸው መግለጻቸውን ሮይተርስ ጨምሮ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ሃምሌ 15 ቀን 2012 ዓ.ም መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በቀጣናው የታየው ወቅታዊ የዝናብ እና የፈሰስ መጠን መጨመር ግድቡን ለመሙላት ሁኔታዎችን አመቺ አድርጓቸው እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በዚያም የተነሳ 4. 9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ የመያዙ ስራ ሃምሌ 15 ቀን መጠናቀቁ ይፋ ከሆነ በኋላ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር ሙሌት 2013 ዓ.ም ክረምት ላይ እንደምትጀምር ገልጻ ነበር፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በመጨው ሃሙስ በኢትጵያ ህሳሴ ግድብ ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሏል፡፡ የግብጽና ሱዳን ባለስልጣናት ስብሰባውን ለመካፈል አቅንተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበኩሏ በግድቡ ዙሪያ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ከሚደረገው ድርድር ውጭ የሌላ አካላት ጣልቃገብነት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡