የሕዳሴ ግድብን ድርድር በማስቀጠል በሁሉም ተቀባይነት ያለው መፍትሔ እንዲገኝ አሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
አቶ ደመቀ በወቅታዊ የኢትዮጵያ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለልዩ ልዑኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል
አቶ ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ ከአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ጋር ተወያይተዋል
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ውይይታቸው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም ዘንድሮ በሚካሔደው 6ኛው ብሔራዊ ምርጫ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
አቶ ደመቀ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔዎች በተለይም በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች እና መልሶ ማቋቋም ረገድ እየተከናወኑ ስላሉ ተግባራት፣ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር አካሄድ ፣ መጪው ብሔራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ ስለተደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች ፣ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ በድርድር እልባት እንዲያገኝ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ፍላጎት በተመለከተ ለልዩ ልዑኩ አስረድተዋቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፌስቡክ ገጹ እንዳስታወቀው ፣ በተያያዘም በኢትዮጵያ እና አሜሪካ መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ አቶ ደመቀ ገጸዋል።
አምባሳደር ጄፍሪ ፈልትማን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ስትራቴክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው፣ በሰላምና መረጋጋት ጉዳዮች በትብብር ለመስራት ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውንም ሚኒስቴሩ ስታውቋል።
አያይዘውም የሕዳሴ ግድብን የሦስትዮሽ ድርድር በማስቀጠል በሁሉም ተደራዳሪ አካላት ዘንድ ተቀባይነት ያለው መፍትሔ ላይ ለመድረስ በሚደረገው ጥረት በሀገራቸው በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
ከሰሞኑ በግብፅ ፣ በኤርትራ እና በሱዳን መሰል የስራ ጉብኝት ያደረጉት አምባሳደር ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የገቡት በትናንትናው ዕለት ሲሆን በዕለቱ ከኢትዮጵያ የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ጋር ተወያይተዋል፡፡
አምባሳደር ፌልትማን ሦስቱ ሀገሮች በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ሁሉን ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ላይ እንዲደርሱ ለመርዳት የሀገራቸውን ቅን እና ገለልተኛ ድጋፍ እንዲሁም ጠንካራ ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ዶ/ር ስለሺ ገልጸዋል፡፡
በጆ ባይደን አስተዳደር በቅርቡ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሸሙት አምባሳደር ፌልትማን በቀጣናው ያሉ አለመግባባቶች ፣ በተለይም የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ እና የኢትዮጵያና የሱዳን የድንበር ውዝግብ ፣ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ለማድረግ በሀገራቸው ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፡፡
አምባሳደሩ በሱዳን በነበራቸው ቆይታ በሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ሦስቱም ተደራዳሪ ሀገራት ካልፈቀዱ በስተቀር አሜሪካ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌላትም ነው የገለጹት፡፡