የውጭ ሀገራት ባንኮች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሳተፍ የሚፈጥረው እድል እና ስጋት ምንድን ነው?
የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱን ተከትሎ መንግስት የሀገር ውስጥ ባንኮች ስትራቴጃቸውን እንዲንዲከልሱ ሲያሳስብ ቆይቷል
መንግስት በአምስት ዓመታት ውስጥ ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ለመስጠት እቅድ ይዟል
በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ባለፉት አመታት ለውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ዝግ ሆነው የቆዩ ናቸው።
በአፍሪካ ሀገራት እና በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚሰራበት ካፒታል ማርኬትን ጨምሮ የኩባንያዎችን ድርሻን የመሸጥ አሰራር በኢትዮጵያ ገና ዳዴ በማለት ላይ ያለ ነው፡፡
የሳፈሪኮም ኩባንያ ወደ ገበያው መግባት እንዲሁም የኢትዮቴሌኮምን ድርሻ ለውጭ ኩባንያዎች ለመሸጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የቅርብ አመታት እንቅስቃሴዎች ናቸው።
በሀገሪቱ የባንኩን ሴክተር ብንመለከት የግል ባንኮች እንዲቋቋሙ እና አገልግሎት እንዲሰጡ ፈቃድ ከተሠጠ ከ32 አመታት የተሻገረ ታሪክ የለውም፡፡
ነሐሴ 28/2014 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባው የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ለማድረግ የቀረበውን ረቂቅ ፖሊሲ አጽድቆ በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑ ይታወሳል።
መንግስት የባንኩን ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ “አገልግሎቶች በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ለመደገፍ፣ የአገሪቱን ምጣኔ ሐብት ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የበለጠ እንዲተሳሰር ለማድረግ ያስችላል።” የሚል እምነት አለው።
ይህን ተከትሎም በርካቶች በዘርፉ ውስጥ የውጭ ባንኮች ተሳትፎ የሚኖረውን ትሩፋት እና ስጋት በተለያየ መንገድ ሲገልጹ ተሰምተዋል።
ሀሳቡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ የሚባል ቢሆነም ከኢትዮጵያ ያነሰ ምጣኔ ሀብት ያላቸው የአፍሪካ ሀገራት ጭምር ከውጭ ባንኮች ጋር መስራት ከጀምሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡
ኬንያ ፣ ሱዳን ፣ ጋና ፣ ናጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ የውጭ ባንኮችን በሀገር ውስጥ በማሳተፍ ጥሩ የሚባል ተሞክሮ ያላቸው ናቸው።
ለመሆኑ የእነኚህ ባንኮች በሀገር ውስጥ ገበያ ውስጥ መሳተፍ የሚኖረው እድል እና ስጋት ምንድን ነው? አልአይን አማረኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ ያለው እድል
የቢዝነስ እና ፋይናንስ አማካሪው ሚካኤል አዲሱ፤ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርአት ደንበኛን ሳይሆን ትርፍን ብቻ መሰረት አድርጎ የተቋቋመ ነው፤ ባለፉት አመታት ባንኮች የመጡበት የቴክኖሎጂ እና የአሰራር መዘመን አዝጋሚ እንደሆነ የሚናገሩት አማካሪው የውጭ ባንኮች በዚህ ረገድ መነቃቃትን እንዲሁም ፉክክርን ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ያምናሉ።
ባንኮቹ ወደ ስራ ሲገቡ ይዘውት የሚመጡት ካፒታል በውጭ ምንዛሪ እና በሀገር ውስጥ ገንዘብ እጥረት ውስጥ ለሚገኝው ኢኮኖሚ ግብአት ሊሆንም እንደሚችል አማካሪው ያክላሉ።
ባንኮቹ ወደ ሀገር ውስጥ ሲመጡ እነርሱን ተከትለው የሚመጡ ኢንቨስተሮች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ተሳትፎ ስለሚኖራቸው ይህም ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ አቅምን የሚጨምር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግዙፍ ኩባያዎችን የመሳብ አቅም እንዳለው ነገር ግን ኢኮኖሚው ዝግ ሆነ የቆየ ኢኮኖሚ እንደመሆኑ በአውሮፓ እና አሜሪካ የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ብለው እንደማይጠብቁ የሚናገሩት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ ናቸው።
ከዛ ይልቅ በአፍሪካ ሀገራት የሚንቀሳቀሱ ባንኮች ቅርንጫፍ በመክፈት እና ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር ተዋህደው ሊሰሩ እንደሚችሉ እምነት አላቸው።
ከፍተኛ ገንዘብ በሚንቀሳቀስባቸው ከተሞች ዙርያ ትኩረት አድርገው የሚሰሩት የሀገር ውስጥ ባንኮች፤ የውጭ ባንኮች መምጣትን ተከትሎ ለአነስተኛ እና ጥቃቅን እንዲሁም የተለያዩ አዳጊ የንግድ እንቅስቀሴዎችን መደጎም እና ብድር ማቅረብ ላይ ትኩረት እንድያደርጉ ሊገደዱ እንደሚችሉ የሚያነሱት የምጣኔሀብት ባለሙያው ይህም ኢኮኖሚውን ሊያሳድግ እንደሚችል እምነት አላቸው፡፡
የሀገር ውስጥ ባንኮች የብድር ስርአት እና የወለድ ምጣኔ ተበዳሪዎችን የሚያበረታታ አይደለም የሚሉት የፋይናንስ እና ቢዝነስ አማካሪው ሚካኤል አዲሱ በበኩላቸው የውጭ ባንኮች መግባት የብድር ወለድ እንዲቀንስ እና ቢዝነስ እንዲበረታታ የሚያደርግ ስለመሆኑ የአቶ ዋሲሁንን ሀሳብ ይጋራሉ።
የባንኮች የወለድ ምጣኔ ፣ ማስያዣ እና ሌሎችም የብድር አሰራሮች ለተገልጋዩ የተመቸ አይደለም የሚሉት አማካሪው፤ የውጭ ባንኮቹ በዚህ ደረጃ በተለያዩ ሀገራት ካላቸው ልምድ ይዘውት የሚመጡት የተሻለ አሰራር የሀገር ውስጥ ባንኮች አሰራራቸውን እንዲከልሱ እና እንዲያሻሽሉ የሚያደርጋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ከባለ አክሲዮኖች በተሰበሰበ ገንዘብ ፣ ከቁጠባ ፣ ከብድር ወለድ እንዲሁም ከአገልግሎት ክፍያ በሚያገኙት ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር በካፒታል የመፎካከር አቅም የላቸውም፡፡
ይህን ለመቋቋም በሀገር ውስጥ ባንኮች በመንግስት ትእዛዝ አልያም በገዛ ፈቃዳቸው ሊዋሀዱ ይችላሉ።ይህም የሰው ሀይል እና የገንዘብ አቅማቸውን በማቀናጀት የተሻለ ቁመና እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው፡፡
የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ መሳተፍ ያለው ስጋት
በስጋት ደረጃ ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የገበያ ጠቅላይነት ወይም ሞኖፖሊ አንደኛው ነው። የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ስራ ሲጀምሩ የቁጠባ ሂሳብ ደብተር አስከፍተው ገንዘብ ሰብስበው ሳይሆን ከራሳቸው ከሚያንቀሳቅሱት ካፒታል በመጠቀም ነው ለደንበኞቻቸው አገልግሎት የሚሰጡት።
በመሆኑም ደካማ የቁጠባ ባህል በሚገኝባት ኢትዮጵያ ዋነኛ የገንዘብ ምንጫቸውን ቁጠባ እና ብድር ያደረጉ የሀገር ውስጥ ባንኮች እንዳይዳከሙ ከውህደት ያለፈ አማራጭ ሊኖር እንደሚገባ የቢዝነስ እና ፋይናንስ አማካሪው አቶ ሚካኤል ይመክራሉ።
አክለውም ባንኮች ደንበኞችን ባማከለ መልኩ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ ማሳደግ ካልቻሉ የሚገጥማቸው ውድድር ቀላል እንደማይሆን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም የውጭ ባንኮች ገንዘብ የሚያስወጡበት እና የሚያስገቡበት መንገድ ላይ የብሄራዊ ባንክ ብርቱ ክትትል ሊያደርግ ይገባል ተብሏል።
በላቲን አሜሪካ የነበረውን የፋይናንስ ቀውስ የውጭ ባንኮች በአንድ ግዜ ነቅለው በመውጣታቸው የተፈጠረ መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ሚካኤል የውጭ ባንኮች በሚያተኩሩባቸው ዘርፎች ላይ ያለውን የገንዘብ ፍሰት መከታተል አሰፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዋሲሁን በላይ በበኩላቸው አንዳንድ ባንኮች የገበያ ድርሻቸውን ሊያጡ ይችላሉ ይህም ትልልቅ ተበዳሪዎች ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ከውጭ ባንኮች ጋር በሚያደርጉት ፉክክር ሊፈጠር የሚችል ነው ባይ ናቸው፡፡
በአንጻሩ የውጭ ባንኮች ትላልቅ ብድር እና ፋይናንስ የሚፈልጉ የኮርፖሬት ደንበኛ በሚል የሚገልጹ ባለሀብቶችን ከሀገር ውስጥ ባንኮች ደንበኝነት ሊያስኮበልሉ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው።ይህ የሚሆነው ደግሞ የውጭ ባንኮቹ ይዘውት በሚመጡት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ካፒታል ምክንያት ነው።
አሁን ባለው ሁኔታ የሀገር ውስጥ ባንኮች በቴክኖሎጂ ፣ በአሰራር ፣ በደንበኛ አያያዝ ፣ በአገልግሎት እና በፋይናንስ አሳታፊነት ክፍተት እንዳለባቸው ሁለቱም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይስማማሉ።በመሆኑም መጪውን የውድድር ጊዜ ለመቋቋም አሰራራቸውን ሊለውጡ እንደሚገባ ይመክራሉ።
ትላልቅ ባለሀብቶች ወይም ተበዳሪዎች ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ አዋጭ ለሆኑ ጥቃቅን ቢዝነሶች ብድሮችን በመስጠት የራሳቸውን ደንበኛ መፍጠር ላይ ሊሰሩ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም እንደ ግብርና እና አገልግሎት ዘርፍ ያሉ ግዙፍ የኢኮኖሚ ምንጮች ላይ በተለየ መንገድ ኢንቨስት በማድረግ የካፒታል አቅማቸውንም ሊያሳድጉ ይገባል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚቀጥሉት ሶስት እና አራት አመታት ከሶስት እስከ አምስት ባንኮች በሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡